ለአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ የአሠራር ማሻሻያ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው።

36

ደባርቅ: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል የተቋማትን መዋቅራዊ ቁመና እና የአገልግሎት ሰጭ ባለሙያዎችን የመፈጸም አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ይገለጻል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ያሬድ አበበ አዲሱ የሲቪል ሰርቪስ የአሠራር ማሻሻያ የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ለማዘመን፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና የመንግሥት ሠራተኛውን ተልዕኮ የመፈፀም አቅም ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ሥራ እና ሠራተኛን ለማገናኘት፣ የአካባቢን የሕዝብ ቁጥር እና የመልማት አቅም ያገናዘበ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡ ዘመኑን የዋጀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለመፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማዕከል ያደረገ ተግባር ለመከዎን እንደሚጠቅምም አስገንዝበዋል፡፡

በዞኑ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የንቅናቄ መድረክ በመፍጠር ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል፡፡ የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ሥራው በአመለካከቱ የበቃ የመንግሥት ሠራተኛን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት የሰው ሃብት አሥተዳደር እና ሕጎች ቡድን መሪ ቴዎድሮስ ጥጋቡ ማሻሻያውን በሚመለከት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው አቀባበልም ጥሩ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች የጠፉ የትምህርት ማስረጃዎች በመኖራቸው ማሰረጃዎቹ እንዲሟሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የሀሰተኛ ትምህርት ማሰረጃ የማጣራት ሥራው ከ96 በመቶ በላይ በኾነ አፈጻጸም እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

አሚኮ ያነጋገራቸው የመንግሥት ሠራተኞችም የአሠራር ማሻሻያው የአተገባበር ሂደት የሚበረታታ እና ጥሩ ጅምር የታየበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሐሰተኛ ትምህርት ማሰረጃ የማጣራት ሥራው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስረጃዎች በተጨማሪ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ያሉ ማሰረጃዎችን ያማከለ ሊኾን እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ማሰረጃ የማጣራት ሥራ በተለያዩ ጊዜዎች ተጀምሮ መቋረጡን የገለጹት ሃሳብ ሰጭዎቹ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የለውጥ አተገባበር ሂደቱ የመንግሥት ሠራተኞችን ሃሳብ በግብዓትነት በማካተት ተፈጻሚነቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየፈተና ውጤት ማስታወቂያ
Next articleሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ ሴት መሪዎች የባሕር ዳር ከተማን የልማት ሥራዎች ጎበኙ።