
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ለረጅም ጊዜ ለግጭት እና ለመከፋፈል መሠረታዊ ምክንያት በኾኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያገባናል የሚሉ አካላት በሠለጠነ መንገድ የሚያደርጉት ውይይት ነው፡፡
ብሔራዊ ምክክር በዋናነት አካታች በኾነ መንገድ የተመረጡ ተዋናዮች በመሠረታዊ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መግባባት ላይ የሚደረስበት እና የውሳኔ ሐሳብ የሚያስቀምጡበት መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል። ሀገራዊ ምክክሮች እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡
በአንድ ሀገር የተከሰቱ የፖለቲካ ችግሮችን ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ እና ለሀገር ሕልውና አስጊ የኾኑ ችግሮችን፣ አለመግባባቶችን በዘላቂነት መፍታት አንዱ ነው። በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመንን ለማስፈን፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር እና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ ሌላኛው ጉዳይ ነው። በዜጎች መካከል የተሻሻለ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ፣ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።
የሀገራዊ ምክክር ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮው ምን ይመስላል?
ሀገራዊ ምክክር ለዓለማችን አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የተካሄዱ ምክክሮችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። በ1989 (እ.አ.አ) በምሥራቅ እና መካከለኛው አውሮፓ ሀገራት የኮሙዩኒዝም መፈራረስ ያስከተለውን ዋና ዋና የፖለቲካ ችግሮች ለመቋቋም ፖላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ምሥራቅ ጀርመን እና ቡልጋሪያ በተከታታይ ጠረጴዛ ዙሪያ ለምክክር ተቀምጠዋል።
ሌላኛው በ1990ዎቹ እንደ ቦሊቪያ እና ኮሎምቢያ ያሉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ሥምምነት የተደረሰባቸው ሂደቶች የሀገራዊ ምክክሮች ቁልፍ ገጽታዎች የተንጸባረቁባቸው እንደኾኑ ይነገራል። በቅርቡ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ከተቀጣጠለው የአረብ አብዮት ጋር በተያያዘ ጎልቶ የታየው ምክክር ነው፡፡ አብዮቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር በመስፋፋቱ በሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን እና የመንም ሀገራዊ ምክክሮችን አድርገዋል፤ በስኬትም በውድቀትም ማሳያ የኾኑ ሂደቶችንም አልፈዋል፡፡
ውስብስብ የለውጥ ሂደቶችን ለመቆጣጠር ምክክርን እንደ መሳሪያ መጠቀማቸው በተቻለ መጠን ባለድርሻ አካላትን ያካተቱ መኾናቸው፣ ምንም እንኳን በእያንዳንዱ ሀገር የነበረው ሂደት ለተለያዩ ተግዳሮቶች ምላሽ የሰጠ ነው። በአብዛኛው በተለምዶ በሀገር ጉዳይ ላይ ውስን ሊሂቃን ብቻ ከሚያደርጉት ውይይት እና ሥምምነት ወጥቶ ከነ ውስንነቱ ማኅበረሰቡን በማካተት ወደ አሳታፊ ፖለቲካ ለመሸጋገር ጥረት የተደረገባቸው መኾናቸው በሂደቶች ውስጥ ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ተደርገው ይወሰዳሉ።
ደቡብ አፍሪካ ያካሄደችው ሀገራዊ ምክክር ደግሞ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ምክክር ትምህርት ሊወሰድባቸው ከሚገቡ ምክክሮች ቀዳሚ ኾኖ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቀምጧል። ደቡብ አፍሪካ በታሪኳ ሁለት የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን አስተናግዳለች። እ.አ.አ ከ1991 እስከ 1993 የተካሄደው “ኮዴሳ” በመባል የሚታወቀው የምክክር ሂደት የመጀመሪያው የሀገሪቱ የምክክር ርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።
ምክክሩ የአፓርታይድ ሥርዓትን ሰላማዊ በኾነ መንገድ በማስወገድ ከዘር መድልዎ ነጻ የኾነች ሀገርን መፍጠር ዋነኛ ዓላማው ነው። ሀገሪቱ በጊዜያዊነት የምትተዳደርበትን ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት ደግሞ ሌላኛው ዓላማ ነበር፡፡ በሂደቱ እጅግ ብዙ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ በር ከፋች መኾንም ችሏል፡፡
ሌላኛው በሀገሪቱ የተተገበረው የምክክር ሂደት እ.አ.አ በ1993 የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት “መልቲ ፓርቲ ኒጎሼሽን ፕሮሰስ – ኤምፒኤንፒ” በመባል የሚታወቀው የድርድር መድረክ ነው። ምክክሩ ቀደም ሲል ተካሂዶ የነበረውን የምክክር ሂደት መሠረት አድርጎ የተነሳም ነው። በዚህም የሀገሪቱ ኀይሎች የተስማሙበትን ጊዜያዊ ሕገ መንግሥት በጋራ ማጽደቅ ተችሏል።
ከሀገሪቱ የምክክር ሂደት ምን መልካም ነገሮች ሊወሰድ ይችላል?
አንደኛው አካታችነት እና አሳታፊነት ነው። በደቡብ አፍሪካ በተደረጉት ሁለቱም የሀገራዊ ምክክር ምዕራፎች የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና የሀሳብ ውክልና በእጅጉ የደረጀ በመኾኑ ሀገሪቱ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የምትችልበትን ቁመና በአነሰ ጊዜ ለማምጣት አስችሏታል፡፡
በምክክር የተሳተፉ የፖለቲካ ኀይሎች መግባባትን ዋነኛ ዓላማ አድርገው ወደ ሂደቱ በመግባታቸው ሌሎች ሀገራት ከሂደቱ ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ትምህርት አስቀምጦ አልፏል፡፡ የምክክር ሂደቱ በሁለት ተከታታይ ዙሮች መካሄዱ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላት ሚዛናዊ ውሳኔዎችን እና አካሄዶችን እንዲከተሉ በር ከፋች ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ ለምክክሩ የተሰጠው ጊዜ ባለድርሻ አካላት ነገሮችን በጥልቀት እና በሰከነ መንፈስ ለማየት ዕድል እንዲያገኙ አድርጓል።
በሀገሪቱ የምክክር ሂደቶች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ተዋናዮች ለሂደቱ መሳካት ያሳዩት ትዕግሥት እና ጽናት ሂደቱን ውጤታማ እና ተቀባይነት ያለው እንዲኾን ማድረጉን በመልካም ተሞክሮነት ተቀምጠዋል። የፖለቲካ ምሁሩ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ለአሚኮ እንዳሉት ምክክር ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ጉዳያቸውን ለመፍታት በስፋት ቢተገብሩትም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባሕሉ ግን ብዙም የተለመደ አይደለም።
አሁን ላይ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ እያደረጋቸው የሚገኙ ምክክሮች ሀገራዊ መግባባት ላይ የሚያደርስ እንደኾነ ነው የገለጹት። እስከ አሁን የተከናወኑ የምክክር ሂደቶችም “ሴኬታማ ናቸው” ይላሉ። ምክክሩ በሀገሪቱ ወረዳዎች ጀምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን እና ባለድርሻ አካላትን ጭምር ያሳተፈ መኾኑ ከአብዛኛዎቹ ምክክር ካካሄዱ ሀገራት የተለየ ያደርገዋል።
በአብዛኛው የዓለም ሀገራት የተካሄደው ምክክር በሀገር አቀፍ ደረጃ ያውም በፖለቲካው እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ላይ የሚገኙ ባለድርሻዎችን ብቻ ያሳተፈ መኾኑን ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ እንደገለጹት ምክክር ብዙ ውስብስብ ችግሮችን መፍታት የሚቻልበት፣ ሁሉም አሸናፊ የሚኾንበት በመኾኑ አሁን ላይ በሀገሪቱ የታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ዋነኛ መፍትሔ ነው።
ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ በንቃት በመሳተፍ ለሀገሩ መፍትሔ ማስቀመጥ ኀላፊነት እንዳለበት መክረዋል። ሀገራዊ ምክክር ከአንድ ወቅት ክንውን ባለፈ ከማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሥራዎች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ መመካከር ባሕል ኾኖ መቀጠል እንዳለበት መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን