ሕዝቡ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሠራ ነው።

14

ሰቆጣ: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰቆጣ ከተማ በሁለት የገጠር እና በሁለት የከተማ ቀበሌዎች የተዋቀረች ናት። አገልግሎት ከሚበዛባቸው ተቋማትም የሰቆጣ ከተማ 02 ቀበሌ አንዱ ነው።

ሼሕ መሐመድ ሀሰን የሰቆጣ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በቀበሌው ያገኙት አገልግሎት ጥሩ ቢኾንም ከሕዝቡ ብዛት አንጻር ረዥም ሰዓት እንደጠበቁ ገልጸዋል።

የቀበሌው መሪዎች በአደረጃጀት ሕዝቡን ማገልገላቸው የሚመሠገን እንደኾነ የተናገሩት ሌላዋ የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ አያል እሸቱ በቀበሌው ሕዝብ መብዛት ለአገልግሎት ባለመመቸቱ ቀበሌው ከሁለት እንዲከፈል ጠይቀዋል።

በ02 ቀበሌ ከ43ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚኖር የቀበሌው ሊቀ መንበር ዲያቆን አክሊሉ ወልዴ ገልጸዋል።

ይህንንም ሕዝብ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ በ142 የልማት ቡድን፣ በ18 ቀጣና እና በስድስት ጣቢያ በማደራጀት ጠንካራ ቀበሌ ለመፍጠር እየሠሩ መኾናቸውን ነው ሊቀ መንበሩ የገለጹት።

የቀበሌው ሕዝብ የሚያነሳውን የቀበሌ ይከፈል ጥያቄ ለምክር ቤቱ አቅርበው ምላሽ እየጠበቁ እንደኾነ የገለጹት ደግሞ የ02 ቀበሌ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ደሳለኝ ፀሐዩ ናቸው።

ከመደበኛ አገልግሎቱ ባሻገር በክረምት ወቅት የበጎ አድራጎት ሥራ፣ የአረንጓዴ አሻራ እና የመንገድ ጥገና ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል።

ፈጣን አገልግሎት ተገልጋዩ እንዲያገኝ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ መኾናቸውን የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉቀን መላኩ ገልጸዋል።

“የከንቲባ ችሎት” በመጀመር ሕዝቡ ቀጥተኛ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉ አበረታች ጅማሮ እንደኾነ የጠቆሙት አቶ ሙሉቀን ሌሎች ተቋማትንም ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ክትትል እያደረጉ መኾኑን አብራርተዋል።

የመንግሥት ሠራተኛውም በተመደበበት የሥራ መስክ በኀላፊነት እና በቅንነት ማኅበረሰቡን እንዲያገለግልም ኀላፊው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የቀጣዩ አምስት ዓመት ዕቅድ እና የ25 ዓመቱ የልማት ፍኖተ ካርታ ለከተሞች ፕላን ትኩረት የሰጠ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next article“ምክክር ከአንድ ወቅት ክንውን ያለፈ ሊኾን ይገባል” ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ