“የቀጣዩ አምስት ዓመት ዕቅድ እና የ25 ዓመቱ የልማት ፍኖተ ካርታ ለከተሞች ፕላን ትኩረት የሰጠ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

42

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ እና የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) አስታውቀዋል።

ዶክተር አህመዲን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የስትራቴጅክ ዕቅዱ የባለፋት አምስት ዓመታትን አፈፃፀም በደንብ በመገምገም እና በመነሻነት በመጠቀም የተዘጋጀ ነው ብለዋል። የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ፍኖተ ካርታውም አማራ ክልል ለወደፊት የሚደርስበትን የልማት ፍላጎት መሠረት ያደረገ፣ ሁሉን አቀፍ የኾነ እና ባለብዙ ዘርፍ ዕቅድ ነው ብለዋል።

ከአኹን በፊት ከነበሩት የተለየ ባሕርይ አለው ያሉት ዶክተር አህመዲን መሐመድ በችግር ላይ ኾነው ለስኬት የበቁትን የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በመቅሰም እና ሳይንሳዊ መንገድን በመከተል የታቀደ ነው ብለዋል። የክልሉን ፀጋ፣ ወግ፣ ባሕል እና እሴቶችንም ያካተተ እንደኾነ አስረድተዋል።

ዘላቂ ሰላምን በማምጣት እና መልካም አሥተዳደርን በማረጋገጥ ላይ ማዕከል ያደረገ እንደኾነም ገልጸዋል። ተተግባሪነቱን በሚያሳይ መልኩ ዕቅዱን የሚመሩትን፣የሚያስፈጽሙትን እና የአፈፃፀም ስልቶችን በሚገባ ለይቶ የተነተነ እንደኾነም ነው ያብራሩት።

የልማት ዕቅዱ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚተገበር በሦስት ክፍሎች የተከፋፈለ እንደኾነም አብራርተዋል። የመጀመሪያው ክፍል ክልሉ ከችግሩ የሚያገግምበት፣ የሁለተኛው ክፍል ለመስፈንጠር መደላድል የሚፈጠርበት እና በሦስተኛው እና በረጅም ጊዜ ደግሞ የቴክኖሎጅ ተወዳዳሪነትን መሠረት በማድረግ አጠቃላይ ብልጽግና የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል።

ከተሜነት እያደገ የሚሄድ የማይቀር ክስተት ነው፤ ከተሞች የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የባሕል እና የቴክኖሎጅ ማዕከል ናቸው፤ ስለኾነም ከተሞች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት እንደኾነም ነው የገለጹት። ከተሞችን ለሥራ እና ለዘላቂ ኑሮ ምቹ ለማድረግ የከተማ መሬትን በአግባቡ ማሥተዳደር እና መምራት፣ የከተማ ፕላን እና የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ማዘመን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የከተማ ፕላን የቀጣዩ ትውልድ ምቹ የኾነ ከተማን ለመፍጠር የሚያገለግል መኾኑን አንስተዋል። የቀጣዩ አምስት ዓመት ዕቅድ እና የ25 ዓመቱ የልማት ፍኖተ ካርታም የከተሞች ፕላንን ትኩረት የሰጠ መኾኑን አመላክተዋል።

ከተሞችን በፕላን ለመምራት የሚያስችል የተቋማዊ አመራር እና የአሥተዳደር ሥርዓት ለውጥ በሚያመጣ መልኩ የሚደራጅበት እና የሚጠናከርበት ይኾናል ነው ያሉት። ቴክኖሎጅ ለከተማ ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፤ ቴክኖሎጅን ተቀብሎ የሚተገብር ማኅበረሰብ መገንባትም ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ የቴክኖሎጅ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ከአኹኑ ጀምሮ መሠረቱን መጣል እና አቅም መገንባት ይገባል ነው ያሉት። አምራች ኢንዱስትሪ ግብርናን፣ ማዕድንን፣ ቴክኖሎጅን እና የሰው ሀብትን በግብዓትነት የሚጠቀም የከተማ ዘርፍ እንደኾነም ገልጸዋል።

ይህንን መሠረት በማድረግም መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ብሎም መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ትኩረት ያደረገ እንደኾነም አንስተዋል። ዕቅዱን ለመፈጸም ጠንካራ የመፈጸም ሥነ ልቦና ያለው ጠንካራ መሪ መፍጠር መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።

ይህንን ለማሳካትም የአመራር ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደኾነ እና በቀጣይም የሰው ኀይል የማደራጀት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል። አማራ ክልል ካለበት ችግር ወጥቶ ተስተካካይ እና ተወዳዳሪ ክልል ኾኖ እንዲቀጥል በሀገራዊ ዕድገትም የጎላ ሚና እንዲኖረው ታስቦ የተዘጋጀ ዕቅድ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

ሕዝባችን ሰላምን እና ልማትን ፈላጊ ነው፣ ሰላሙን ማስቀጠል እና ሙሉ በሙሉ ሰላሙ የተረጋገጠ ክልል እንዲኾን ሕዝቡ ሚናውን እንዲወጣ ዶክተር አህመዲን መሐመድ አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ፍኖተ ካርታ ያዘጋጀ መኾኑን መላው ሕዝብ ከወዲኹ አውቆ ለተግባራዊነቱ በሀብት፣ በጉልበት እና በሀሳብ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበቂ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት መኖሩን የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleሕዝቡ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሠራ ነው።