
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ለ2017/18 የመኸር ምርት የሚኾን 315 ሺህ 539 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ዝግጁ መኾኑን የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ ለአሚኮ ተናግረዋል።
የአንደኛ ዙር እርሻ ሙሉ በሙሉ ተከናውኗል ያሉት አቶ በለጠ ሁለተኛ ዙር 91 በመቶ፣ ሦሥተኛ ዙር 80 በመቶ የእርሻ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል። የክልሉን ምርት ጭምር ከፍ በሚያደርጉ ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር እና ቦሎቄን በመለየት እና በኩታ ገጠም በማረስ 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን ከአጠቃላይ ሰብልም 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የእርሻ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። 86 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈኑንም አቶ በለጠ ተናግረዋል።
ለምርት ዘመኑ 1 ሚሊዮን 266 ሺህ 232 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል ያሉት አቶ በለጠ 480 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ በማስገባት በሰባት ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ብለዋል።
በዞኑ ቀድሞ ለሚዘራው በቆሎ 260 ሺህ ኩንታል ዳፕ ለማሰራጨት ታቅዶ 300 ሺህ ኩንታል ተሰራጭቷል ነው ያሉት። የአፈር ማዳበሪያ በመጓጓዝ ላይ በመኾኑ ለሌሎች ሰብሎች በወቅቱ ይደርሳል ብለዋል።
የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር የለም ያሉት አቶ በለጠ በዞኑ 21 የምርጥ ዘር አቅራቢዎች ይገኛሉ ነው ያሉት። 17 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ብለዋል። ለሌሎች የሰብል ዓይነቶችም ምርጥ ዘር በወቅቱ ለማሰራጨት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርን እና የአፈር ማዳበሪያን በግብርና ሙያተኞች ምክረ ሐሳብ መሰረት መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል። የተባይ አሰሳ እና የሰብል እንክብካቤ በማድረግ ለየት ያለ ችግር ሲገጥማቸው ለባለሙያዎች እንዲጠቁሙም ጥሪ አቅርበዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን በደቡብ አቸፈር ወረዳ የዲላሞ ዙሪያ ነዋሪው አርሶ አደር ምትኩ ጎበዜ የሚፈልጉትን ያህል የበቆሎ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በመግዛት 1 ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የአንዳሳ ዙሪያ ነዋሪ አርሶ አደር ሳሉዓለም ከበደ የአፈር ማዳባሪያ እና የበቆሎ ምርጥ ዘር እንደቀረበላቸው ተናግረዋል። ሌሎችም የምርጥ ዘር ዓይነቶች በወቅቱ እና በፍላጎታቸው መሠረት እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን