
ደብረ ታቦር: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና በመጀመሪያው ዙር ከ10 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ለማስፈተን ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አሥራቴ ተናግረዋል።
በጸጥታው ችግር በሁለተኛ ዙር ተመዝግበው ትምህርት የጀመሩ ከ1 ሺህ 100 በላይ ተማሪዎችም በቀጣይ ፈተናውን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል። ለዚህም ተገቢውን ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ነው የተናገሩት። በሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተውጣጡ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቤተ መጻሕፍት ከሰኞ እስከ ሰኞ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን እና የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው በዘርፉ ባለሙያዎች መሠራቱን ገልጸዋል። ፈተናው ሰላማዊ በኾነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ግብረ ኀይል መቋቋሙን የገለጹት አቶ ደስታ ተማሪዎች ከየወረዳቸው መጥተው በሚፈተኑበት ዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ ደኅንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የየወረዳዎች ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች እና የትምህርት ቤቶች ርእሳነ መምህራን ለተማሪዎች አስፈላጊውን ግንዛቤ እንዲፈጥሩ መምሪያ ኀላፊው አሳስበዋል። ፈተናውን በስኬት ለማጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጥምረት በመሥራት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን