በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ችግኞች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታቸው ምን ያክል ነው ?

46

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ትኩረት በመሰጠት አረንጓዴ ምጣኔ ሀብትን ለመፍጠር እየተሠራ ነው። ለዚህም ከ2011 ዓ.ም የክረምት ወቅት ጀምሮ በየዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ እየተተገበረ ይገኛል።

በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በየዓመቱ ችግኞች ሲተከሉ ቆይተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት እንድትኾን አስችሏታል። በአማራ ክልልም አረንጓዴ አሻራ በሰፊ ንቅናቄ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡

ለመኾኑ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ምን ያክል ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ እንዲኖረው ታስቦ እየተሠራ ይኾን? በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የሚተከሉ ችግኞች የሚዘጋጁት ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታቸው ተመዝኖ ነው ይላሉ፡፡

ከምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ አንጻር ሁሉም የሚተከሉ ችግኞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡በአረንጓዴ አሻራ ከሚተከሉ ችግኞች መካከል በዋናነት ዋንዛ፣ ባሕር ዛፍ እና መሰል ዛፎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

የደን ሽፋንን ሊያሳድጉ የሚችሉት እነዚህ ችግኞች በአብዛኛው ለማገዶ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለኢንዱስትሪ ሥራ እና ለኤሌክትሪክ ምሰሶነት በመዋል ከፍ ያለ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያስገኛሉ ብለዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ችግኞች ሲዘጋጁ እያንዳንዱ የዛፍ ባህሪ ለየትኛው የአየር ሁኔታ ተብሎ ተጠንቶ የሚዘጋጅ ነው።

ከአጠቃላይ ከሚተከሉት ችግኞች የእንጨትነት ባሕሪ ያላቸው ከ60 እስከ 75 በመቶ የሚኾነውን ድርሻ እንዲይዙ መደረጉ የሚያሳየው የሚተከሉ ችግኞች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታቸው እየታየ እንደሚተከሉ ነው ብለዋል።

ሌላው የጥምር ደን እርሻን ታሳቢ ተደርገው የምርት እና ምርታማነትን፣ የአፈር ለምነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ከሰብል እና ከእንስሳት ጋር ተጣጥመው የሚሄዱ የዛፍ ዝርያዎች እንዲተከሉ ሲደረግ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

ከሰብል ጋር ተጣጥመው እንዲተከሉ የሚደረጉት እንደ ብሳና እና የፍራፍሬ ተክሎች ቅጠላቸው መሬት ላይ ሲያርፍ የመሬቱን የአፈር ለምነት የሚጨምሩ እንደኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ ለአካባቢ ጥበቃ በተለይም ለተራቆተ እና ለተጋጋጠ መሬት ተብለው የሚተከሉ የሳርነት ባህሪ ያላቸው እና ለእንስሳት መኖነት ታሳቢ ተደርገው የሚተከሉት ችግኞች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የሚተከሉት ችግኞች የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው በመኾኑ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ሚናቸው ከፍተኛ መኾኑንም አስረድተዋል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚተከሉ ችግኞች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደኾኑም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“እንግዳ ተቀባዩ የጅማ ሕዝብ ላደረገልን የሞቀ አቀባበል እናመሰግናለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleበግጭቱ ምክንያት ጉዳት የገጠማቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።