
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳርን ከኢትዮጵያ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውብ፣ ለኑሮ ተመራጭ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ትልልቅ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ የተጀመሩ ከ20 እስከ 40 ሜትር ስፋት ያላቸው 22 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገዶች ግንባታዎች ተጠቃሽ ናቸው። 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። መንገዶቹ የሳይክል፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ መንገዶችን ያካተቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ እውን የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። በከተማዋ የሚሠሩ የኮሪደር ልማት እና መንገዶች የሳይክል ስፖርቱን የሚያሳድጉ መኾኑን ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደገለጹት የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት ለማሳደግ በመንግሥት እየተሠሩ ከሚገኙ ሥራዎች ባለፈ በግል ባለሀብቶች ጭምር ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የጣና ማሪና ኢኮ ቱሪዝም ግንባታ አንዱ ነው። ድርጅቱ አሁን ላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የሚሳድጉ አራት ዘመናዊ ፈጣን ጀልባዎችን ወደ ሥራ አሥገብቷል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በመጓጓዝ ላይ የምትገኘው ጣናነሽ ሁለት ወደ ሥራ ስትገባ ደግሞ ባሕር ዳርን ከጎርጎራ እና ጎንደር ጋር በባሕር በማስተሳሰር የቱሪዝም ዘርፉ እንዲሻሻል የሚያደርግ ነው። ባለ አምስት ኮኮብ እና ከዚያ በላይ ደረጃ ያላቸው ሰባት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ግንባታ ፈቃድ ለባለሀብቶች የቦታ ርክክብ መደረጉንም ገልጸዋል።
የከተማዋን ደኅንነት ለማረጋገጥ ካሜራዎችን የመግጠም ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።አሁን ላይ ባሕር ዳር በተፈጠረው ሰላም 234 ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ እና ከ200 በላይ ደግሞ በግንባታ ላይ መኾናቸውንም ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን