
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሕገ ወጥ መንገድ የተከዘነ የምግብ እህልና ናፍጣ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮማንደር ጌትነት መስፍን ከሕዝቡ የተሰጠውን ጥቆማ በመቀበል በተደረገው ፍተሻ ከ1 ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ እና በቆሎ በአብማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01 ውሰታ የገበያ ማዕከል መጋዘን ውስጥ ተከዝኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
እንደዚህ ያሉ ሕገወጥ ተግባራት የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብሱ የገለጹት ኀላፊው በሕገወጥነት የሚከዘኑ የምግብ እህሎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይም በተደረገው ሕገ ወጥነትን የመከላከል ተግባር በቁይ መስመር ሊወጣ የነበረ ከ3 ሺህ ሊትር በላይ ናፍጣ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮማንደር ጌትነት መስፍን ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ሕግ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ለፖሊስ የመጠቆም ልምዱን አጠናክሮ በማስቀጠል ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ተባባሪ እንዲኾንም ኀላፊው አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን