የንግዱ ማኅበረሰብ ቫት በመቁረጥ እና የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ።

15

ሰቆጣ: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው አቶ አሰፋ አዳነ ታታሪ ነጋዴ ናቸው።አቶ አሰፋ አዳነ የጅምላ ሸቀጣሸቀጥ አከፋፋይ ሲኾኑ ግብራቸውን በሰዓቱ በመክፈልም ይታወቃሉ።

የሀገርን ልማት ለማፋጠን ግብርን በወቅቱ መክፈል የብልህ ነጋዴ መገለጫ ነው የሚሉት አቶ አሰፋ ቫት በመቁረጥ የሕዝብ እና የመንግሥትን ሀብት እንደሚሠበሥቡ ነው ያስረዱት።

ለተረካቢዎች በደረሰኝ እንደሚያከፋፍሉ የጠቆሙት አቶ አሰፋ ሌሎችም ቫት በመቁረጥ እና የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ሕገ መንግሥቱ የጣለባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ ታረቀ በ2017 የበጀት ዓመት 181 ሚሊዮን 337 ሺህ 963 ብር በመደበኛ ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ 192 ሚሊዮን 141 ሺህ 317 ብር ገቢ መሠብሠብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ የዕቅዱን 105 በመቶ ማሳካቱንም ጠቁመዋል። ቫት በመቁረጥ እና ታክስ በመክፈል በኩል ክፍተት እንዳለ የገለጹት አቶ ሙሉጌታ በቀጣይም የከተማ ልማት ገቢያቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሠሩ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ አበባው ከኾነ በተያዘው ዓመት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 743 ሚሊዮን 519 ሺህ 216 ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ በ10 ወር ብቻ 601 ሚሊዮን 192ሺህ 148 ብር መሠብሠብ መቻሉን ተናግረዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የዕቅዱን 81 በመቶ ማሳካት እንደቻለም ኀላፊው አብራርተዋል። በቀጣይም ተገልጋዩ ደረሰኝ በመቁረጥ መንግሥት እና ሕዝብ ሊያገኝ የሚገባውን የቫት ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ የንግዱ ማኅበረሰብ ቫት እንዲቆርጥ አሳስበዋል። ቫት በማይቆርጡ ሰባት ነጋዴዎች ላይ የገንዘብ እና የፈቃድ ማገድ የእርምት ርምጃ እንደተወሰደም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀመር ያብራሩት የመምሪያ ኀላፊው ለዚህም የንግዱ ማኅበረሰብ በሚገባ ግብሩን አስቦ እንዲከፍልም ነው ያሳሰቡት።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው እና ለደን ልማት የሚውሉ የዕጽዋት ዝርያዎችን እያዘጋጀ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገለጸ።
Next articleበሕገ ወጥ መንገድ የተከዘነ የምግብ እህል እና ናፍጣ በቁጥጥር ስር ዋለ።