የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ጀመሩ፡፡

460

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዩኒቨርሲቲዎች የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ እያደረጉ ነው፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ግን በዚህ ክረምት አያጠናቅቁም፡፡

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ትምህርቱን የሚከታተሉበትና ከአማካሪዎቻቸው ጋርም የሚገናኙበት ምቹ ሁኔታ በመኖሩ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ እንደጀመሩ ታውቋል፡፡ በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ኤባ ሚጀና (ዶክተር) የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ባይኖርም ጅማ እና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ትምህርት ማስጨረስ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ትምህርታቸውን የማይጨርሱ ተማሪዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።

የመጨረሻ ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በወረርሽኙ ምክንያት ባለመማራቸው፣ አንዳንዶችም የመጀመሪያ መንፈቅ ፈተና ባለመፈተናቸው በዚህ ክረምት ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ እንደማይኖሩም ዶክተር ኤባ አስታውቀዋል፡፡

የተማሪዎቹን ቀጣይ ሁኔታ በተመለከተም ወረርሽኙ ቢቆም ምን መደረግ እንዳለበት በየሳምንቱ ከየትምህርት ተቋማቱ የትምህርት አመራሮች ጋር ግምገማ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርት እንዲቋረጥ ሲደረግ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው በቤታቸው የሚማሩባቸውን የትምህርት ሰነዶች እንዲሰጧቸው የሚል አቅጣጫ ተሰጥቶ እንደነበርም አመልክተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘዴ ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና ጥረቱ ተማሪዎች ጊዜያቸውን እንዲጠቀሙ እንጂ ወደሚቀጥለው የትምህርት ምዕራፍ እንዲያልፉ የሚረዳቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታም ተማሪዎች በየትምህርት ተቋማቶቻቸው የሚላኩላቸውን ሰነዶች በማንበብ እንደሚቆዩ አስታውቀዋል።

የመጨረሻ ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ደግሞ ከየትምህርት ተቋሞቻቸው የሚላኩላቸውን የትምህርት ሰነዶች እያነበቡ እንደሚቆዩ ኢፕድ ዘግቧል፡፡

Previous articleወረርሽኙን ሰዎችን ከሃይማኖታቸው ለመነጠል የተፈጠረ አስመስሎ ሰውን ማዘናጋት ተገቢ አለመሆኑን ግብረ ኃይሉ አሳሰበ።
Next articleበ24 ሰዓታት ውስጥ በ137 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቷል፡፡