ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው እና ለደን ልማት የሚውሉ የዕጽዋት ዝርያዎችን እያዘጋጀ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገለጸ።

16

ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው እና ለደን ልማት የሚውሉ የዕጽዋት ዝርያዎችን ለክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እያዘጋጀ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል። መምሪያው ለተከላ የሚኾን የቦታ መረጣና የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል።

ለክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በማኅበረሰቡና በመንግሥት ችግኝ ጣቢያዎች ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዕጽዋት ዝርያዎችን እያለማ ይገኛል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮነን እስካሁን በአረንጓዴ አሻራ እና በመደበኛ የችግኝ ተከላ በተሠራው ሥራ ውጤት መምጣቱንና በዞኑ ያለው የደን መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ለችግኝ ተከላ የሚውል የቦታ ልየታና ጉድጓድ የማዘጋጀት ሥራ ተጀምሯል ብለዋል። ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው እና ለደን ልማት የሚውሉ የዕጽዋት ዝርያዎችን እያዘጋጁ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የሚተከሉ ዕጽዋትን የመጽደቅ ምጣኔ ከፍ ለማድረግ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ17 ወረዳዎች የተመረጡ የደን ቦታዎችንም የመለየት ሥራ ተጠናቅቋል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጽናት የመሥራት፣ በማሳ የመተጋገዝ ባሕል በሁሉም አካባቢ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየንግዱ ማኅበረሰብ ቫት በመቁረጥ እና የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ።