በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ጥራት የሚያሳድጉ መኾናቸውን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።

13

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኀላፊ እና የቡድኑ አሥተባባሪ ሐፍታይ ገብረ እግዚአብሔር እንዳሉት በባሕር ዳር ከተማ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚያላብሱ ናቸው።

በተለይም በጣና ዳር እየተሠሩ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶች እና አረንጓዴ ልማቶች የኮንፈረስ ቱሪዝምን የሚያሳድጉ፣ ለአረንጓዴ ልማት የተሠጠውን ትኩረትም እውን ያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የዓባይ ድልድይ ከመተላለፊያነት ያለፈ በዘመኑ በዓባይ ወንዝ ላይ ከተሠሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች አንዱ እና ለባሕር ዳር ከተማም አርማ የሚኾን፣ የቱሪዝም መዳረሻ ኾኖ የሚያገለግል መኾኑን ገልጸዋል።

የተሠሩት ሥራዎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚሠሯቸውን ፊልሞች፣ የቪዲዮ ክሊፖች እና ሌሎች ሥራዎችን ጥራት የሚያሳድጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። የከተማዋ ልማት ይበልጥ እንዲስፋ ሁሉም ለሰላም መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት ደግሞ ባሕል ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንደመጡ የነገሩን ምህረት ምትኩ በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ተፈጥሮ ይበልጥ ውበት የሚያላብስ መኾኑን ገልጸዋል። የተሠሩ ሥራዎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ሥራዎች የሚያሳድጉ በመኾናቸው የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

ሌላኛው የኪነ ጥበብ ባለሙያ ወንድሙ ከበደ እንዳሉት ታላቁ ጣና ሐይቅ እና የዓባይ ወንዝ ለከተማዋ ልዩ ገጽታ ያላበሷት ውብ ከተማ ናት።የተሠሩ ታላላቅ የልማት ሥራዎች ደግሞ የተፈጥሮ ውበቷ ይበልጥ እንዲደምቅም አድርጓል ብለዋል። የከተማዋን ልማት ለማስቀጠል ሁሉም በሙያው ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋን ከኢትዮጵያ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውብ እና ተመራጭ ለማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ትልልቅ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች፣ የኮሪደር ልማቶች እና አረንጓዴ ልማቶች እየተሠሩ ከሚገኙት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።

የልማት ሥራዎቹ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጥበባቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ ተደርገው የተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ባለሙያዎች ጥበባቸውን ተጠቅመው የማስተዋወቅ እና የሕዝቦችን ትስስር የማጠናከር ሥራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ባለሃብቶች በከተማዋ እንዲያለሙ፣ ጎብኝዎች ደግሞ ከተማዋን እና አካባቢውን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦‎ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግርን እየፈታ የሚገኘው ፋብሪካ
Next article“የቀደመ ታሪኳን የበለጠ የሚያደምቅ ሥራ ጅማ ላይ እየተሠራ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ