
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ባላት በእንስሳት ሃብት አቅም ከአፍሪካ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ አማራ ክልል ከቀዳሚዎቹ ውስጥ ይመደባል።
ክልሉ ለዳልጋ ከብት፣ ለዶሮ፣ ለፍየል ሃብት ልማት ምቹ እንደኾነም ይነገራል። ይሁን እንጂ የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ደረጃ ዝቅተኛ መኾኑን ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚናገሩት።
የእንስሳት ሀብቱ ምርታማነትን ለማረጋገጥ እና ዘርፋ የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲያበረክት ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች መካከል የተሻሻለ የመኖ አቅርቦት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
በዘርፉ ውጤት ለማምጣት ከዘልማዳዊ አሠራር ወጥቶ ዘመናዊ የመኖ አቅርቦት ላይ በስፋት ማተኮርን ይጠይቃል። የእንስሳት መኖ በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት ለእንስሳት ሀብት ልማት ግንባር ቀዳሚ ተግባር እንደኾነም ነው የሚገለጸው።
የእንስሳት መኖ አጠቃላይ ለእንስሳት ሀብት ልማት ተግባር ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከ60 እስከ 80 በመቶ እንደሚይዝ የእንስሳት ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የመኖ አቅርቦትን በጥራት እና በብዛት ማከናዎን የእንስሳት ሀብትን ምርታማነት በማሳደግ እንደ ሀገር የተያዘውን የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በ2015 ዓ.ም በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጭ በባሕር ዳር ከተማ ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው ሙሌ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የመኖ አቅርቦት ችግርን እየፈታ መኾኑ ተገልጿል። አንድ ብርጭቆ ወተት እና አንድ እንቁላል ለአንድ ሰው የሚል መርህ ይዞ የተነሳው የእንሰሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለዘርፉ ትልቅ አጋዥ ኾኗል።
የመኖ ማቀነባበሪያው ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ የእንስሳት ልማት አልሚዎች በቅርብ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ነው ተጠቃሚዎች የሚናገሩት።
በዶሮ እርባታ የተሠማሩት መኳንንት የአማኑኤል እና ጓደኞቻቸው የኅብረት ሥራ ሽርክና ማኅበር በአሁኑ ሰዓት 2ሺህ 300 ዶሮዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል።
የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ መኳንንት በዕውቀት ከአኹን በፊት ለዶሮዎች መኖ የሚያስመጡት ከአዲስ አበባ እንደነበር አስታውሰዋል። ከአዲስ አበባ ለማስመጣት በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ የመጓተት ችግሮች ይገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ሙሌ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በባሕር ዳር ከተማ ከተገነባ በኋላ ግን በቅርበት ማግኘት በመቻላቸው ሥራውን ቀላል እንዳደረገላቸው አብራርተዋል።
ፋብሪካው የሚያመርተው ምርት በአቅርቦት ደረጃ ጥሩ መኾኑን ገልጸዋል። በጥራት በኩል ግን ውስንነት እንዳለበት ነው ያነሱት። በተለይም ለዶሮ የሚኾን መኖ ወጥ ጥራት እንደሌለው ነው የገለጹት።
በባሕር ዳር ከተማ በወተት ላም እርባታ ዘርፍ የተሰማሩት አበበ ወርቁ ከሙሌ የዘመናዊ መኖ ማቀነባበሪያ ፍብሪካ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነግረውናል።
እርሳቸውም ከአሁን በፊት ከሌላ ቦታ ያስመጡ እንደነበር ገልጸዋል። የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በባሕር ዳር ከተማ መገንባቱ ብዙ ጫናዎችን እንዳቃለለላቸው አንስተዋል።
ለወተት ላም ተስማሚ የኾነ መኖ ከፋብሪካው እያገኙ መኾኑንም ነው የገለጹት። አኹን ላይ የመኖ ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ መኖውን በሥፋት ለመጠቀም እንደተቸገሩም ገልጸዋል።
የፋብሪካው ባለቤት በኾነው ኤም.ኤስ.ኤ ቢዝነስ ግሩፕ የዲጂታል ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ተስፋ ጥበብ ፋብሪካው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተዋቀረ እና ከእጅ ንክኪ ሙሉ በሙሉ ነፃ የኾነ መኾኑን አንስተዋል።
የሚያመርተው ምርት ከፍተኛ ጥራት ያለው እና በአጭር ጊዜ ውጤት የሚያመጣ መኾኑን ነው የገለጹት። ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃም ተደራሽ እየኾነ የመጣ መኾኑን አንስተዋል። በዘርፉ ከፍተኛ ሙያ ያላቸውን የውጭ ባለሙያዎችን ቀጥሮ በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እያመረተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የጥራት ችግር አለበት በሚል ለሚነሳው ጥያቄ የአጠቃቀም ችግር እንደኾነ ገልጸዋል። ተጠቃሚዎች ምርቱን ከሌላ መኖ እና ተረፈ ምርት ጋር ስለሚጠቀሙበት ውጤት የማያመጣ እና ምርቱ የጥራት ችግር ያለበት እንደሚያስመስለው አንስተዋል።
ምርቱ ከሌላ መኖ ጋር ተቀላቅሎ ጥቅም ላይ ከዋለ ውጤት እንደማያመጣ በጥናት አረጋግጠናል ብለዋል። ተጠቃሚዎች ምርቱን ሳይቀላቅሉ ብቻውን መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ለአብነትም የእኛን ምርት ብቻ የሚጠቀም ከኾነ አንድ በሬ በሁለት ወር ውስጥ እንደሚያደርስ አረጋግጠናል ብለዋል። በተመሳሳይ በወተት ላም እና በዶሮ እርባታም በተመሳሳይ ውጤት አለው ነው ያሉት።
በየወቅቱ ለአከፋፋዮች እና ለኢንተርፕራይዞች ስለአጠቃቀሙ ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ጥራት ላይ መሠረት ተደርጎ ስለሚመረት ዋጋው ከሌሎቹ የመኖ ምርቶች አንፃር ሲታይ ውድ መኾኑንም አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ የሚመረትበት ግብዓት፣ የሚጠቀመውን ቴክኖሎጅን እና የጥራት ደረጃውን ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም አንስተዋል።
ፋብሪካው በእንስሳት ሀብት ልማት ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት።
በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ዘርፉን የሚያስተባብሩ እና የሚመሩ አካላት ኹሉ ከፋብሪካው ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት የመኖ ልማት እና አጠቃቀም ባለሙያ አበበ ምትኬ ከአምስት ዓመት በፊት በክልሉ የእንስሳት የመኖ ማቀነባበሪያ እንደማይታወቅ እና መኖ ከክልሉ ውጭ ይመጣ እንደነበር አስታውሰዋል።
አኹን ላይ በክልሉ 35 የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በዚህም ከክልሉ አልፎ ለሌሎች ክልሎች የሚተርፍ መኖ እየተመረተ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ካሉት ፋብሪካዎችም በባሕር ዳር ከተማ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ሙሌ መኖ ማቀነባበሪያ ፍብሪካ ግንባር ቀደም መኾኑን ጠቅሰዋል።
ፋብሪካው በክልሉ ያጋጥም የነበረውን የእንስሳት መኖ እጥረት እየፈታ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት። በክልሉ በእንስሳት ልማት ዘርፍ ለተሰማሩት አንቀሳቃሾች በጥራት እያቀረበ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን