
አዲስ አበባ: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ በጅማ ከተማ ተጀምሯል።
በዚህ ውድድር ከክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ከ4ሺህ 500 በላይ ልዑካን ተሳታፊ ናቸው። ስፖርተኞች በ26 የስፖርት ዓይነቶች ይፎካከራሉ።
የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ከዘጠኝ ዓመታት መቋረጥ በኋላ በዚህ ዓመት ነው ወደ ውድድር የተመለሰው።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የተቋረጡ ውድድሮች በዚህ ዓመት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በሀገሪቱ በተጀመረው ሪፎርም ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ስፖርት መኾኑን ገልጸዋል።
ስፖርት ለአንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መኾኑን ነው ያነሱት። ከዘርፉ የበለጠ ለመጠቀም በጥናት ላይ የተመረኮዘ ስትራቴጂ በመንደፍ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የስፖርት ልማትን ለማሳደግም በየደረጃው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የኾኑ ከአነስተኛ የጥርጊያ ሜዳዎች ጀምሮ ትላልቅ ዓለም አቀፋዊ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታ እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታትም መካከለኛ እና አነሰተኛ ቁጥር ያላቸው ከ14ሺህ በላይ ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸው ተመላክቷል።
ስፖርቱን ለማሳደግ እና የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር መላው ኢትዮጵያን ጨምሮ ተቋርጠው የቆዩ ውድድሮችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲመለሱ ማድረጉን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “ስፖርት የነገዋን የኢትዮጵያ ዜጎች መፍጠሪያችን ነው” ብለዋል።
ስፖርት በሁሉም መንገድ የነቃ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
ስፖርት ከውድድር እና ጤናን ከመጠበቅ በተጨማሪ የሕዝብ አንድነት እና ትስስርን ለማጠናከር አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
6ኛው የመላ ኢትዮጵያ ውድድር ከሰኔ 10/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 19/2017 ዓ.ም በጅማ ከተማ ይካሄዳል።
ዘጋቢ፦ባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን