
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስድስተኛው የመላው ኢትዮጵያ ስፖርት ጨዋታ በጀማ ከተማ ተጀምሯል። በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት ያጋሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሀገር አቀፍ የስፖርት ጨዋታዎች ሕዝቦችን የማስተሳሰር አቅም ያላቸው ናቸው ብለዋል። የነገ የሀገር ዘዋሪ ወጣቶች ሀገራቸውን እና ባሕላቸውን የሚያውቁበት ዕድል የሚፈጥርበት መድረክ መኾኑንም አንስተዋል።
“ስፖርት ለኅብረ ኢትዮጵያ አርበኝነት” በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በጅማ ከተማ የተዘጋጀውን ስድስተኛው የመላው ኢትዮጵያ ስፖርት ጨዋታን አስጀምረናል ብለዋል።
መሪ ቃሉን በትክክል በምትገልጸው እና ለዘመናት የኅብረ ብሔራዊነት መናኸሪያ በኾነችው በአባ ጅፋር ሀገር ጅማ የተጀመረው የስፖርት ጨዋታ፤ ወጣት ስፖርተኞቻችን አስፈላጊ የሕይዎት ክሀሎቶችን፣ አካታችነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ የቡድን ሥራን እና ኀላፊነትን እንዲያዳብሩ ዕድል የሚፈጥር እንደኾነም ጠቁመዋል።
“ስፖርት የነገዋን ኢትዮጵያ ዜጎች መፍጠሪያችን ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነቃ እና የበቃ ትውልድ የምናፈራበት መስክ እንደኾነም ጠቁመዋል። ለዚህም በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በአነስተኛ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ እየገነባን እንገኛለን ነው ያሉት።
አንዱ አብነት ደግሞ ዛሬ ያስጀመርነው እና በተለያዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ጉልህ ማሳያ ነው ብለውታል።
በዚህ ስፖርታዊ ጨዋታ ለተሳተፋችሁ የክልል እና የከተማ አስተደዳሮች፤ የውድድር አዘጋጅ ለኾነው የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ለኦሮሚያ ክልልና ለጅማ ከተማ፣ ያለኝን ምስጋና በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ ነው ያሉት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!