
ጎንደር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጎርጎራ በአረንጓዴ ዕፅዋት ተሸፍኖ፣ በወፎች ዝማሬ ደምቆ፣ ጣና ሐይቅን ተንተርሶ የሚገኝ ውብ ቦታ ነው።
ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የጎርጎራን ኢኮ ቱሪዝም ድባብ በቀን እና በምሽት ጎብኝተዋል።
ጎርጎራ የተፈጥሮ ችሮታ፣ በሰዎች አዕምሮ ተገልጦ ሀሴትን የሚያላብስ ልዩ የመስህብ ቦታ እንደኾነ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ደራሲ ግርማይ ከበደ ጎርጎራን ለረዥም ጊዜ እንደሚያውቋት ገልጸዋል። አሁናዊ ገፅታዋ ደግሞ ከጠበቅሁት በላይ ነው ይላሉ። ጎርጎራ ቁጭት በስኬት ድል የኾነበት ፕሮጀክት መኾኑንም ተናግረዋል።
ጎርጎራን የኪነ ጥበቡ ቤተሰብ ተሰባስቦ ማየቱ በቀጣይ ለጋራ ዕጣ ፈንታችን በጋራ መሥራት እንደሚገባን ማሣያ ነው ብለዋል።
አርቲስት ብርቱካን ጂማ ደግሞ ወደ ውጭ ሀገር ስንሄድ የምናያቸው ቦታዎች እና ውበታቸው ምነው በሀገራችን በኾነ ብለን ስንመኝ የነበረውን በኢትዮጵያ በማየታችን የሚያኮራ ነው ብለዋል። ተፈጥሮን ጠብቆ የተሠራበት መንገድም አስደማሚ መኾኑን ገልጸዋል። አርቲስቷ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣን የጥበብ ሰዎች በመኾናችን አካባቢውን ለመጠቀም፣ ለማስተዋወቅ እና ማኅበረሰብን ለማስተሳሰር በሙያችን እንሠራለን ብለዋል።
የባሕል አምባሳደሯ ቤተልሄም ዘርጋው ጎርጎራን በመገናኛ ብዙኀን ከመመልከት በላይ በቦታው ተገኝቼ ማየቴ ልዩ ድባብ እንዳለው ተመልክቻለሁ ነው ያለችው። የሥራው ጥራትም አስደናቂ እንደኾነ ተናግራለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የቡድኑ አስተባባሪ ሓፍታይ ገብረ እግዚአብሔር ጎርጎራ ብዙ የተቀኙላት ትንሿ የኢትዮጵያ መልክ ናት ብለዋል።
አካባቢው ለረዥም ዓመታት የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኖሪያ በመኾኑ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ያስተሣሠረ እንደኾነ አንስተዋል። ጎርጎራ የመሥራት እና የመቻል አቅም የታየበት ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ፕሮጀክት መኾኑን አንስተዋል።
ጎርጎራ የአርክቴክት ጥበብ ከፍታ የታየበት ፕሮጀክት መኾኑን የጠቀሱት አቶ ሓፍታይ የኪነ ጥበቡ ማኅበረሰብ ለዓለም ለማስተዋወቅ አካባቢው የቱሪስት መናኻሪያ እንዲኾን መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ሰፊ ታሪክ፣ ልዩ ውበት ያላት ሀገር በመኾኗ ሌሎች ያልታዩ ቦታዎችን እየገለጡ ማልማት፣ ቀጣይም ከመንግሥት ብቻ ሳይኾን ከባለሀብቱ እና ከሕዝቡ የሚጠበቅ እንደኾነ አብራርተዋል።
ዘገቢ:- አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን