
የአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ወረርሽኙን ለመከላከል እየተሠሩ ባሉና ቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ማምሻ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው ላይ እንደተመላከተውም ወረርሽኙ በምዕራብ ጎንደር አካባቢ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድርና የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ እንደተናገሩት በምዕራብ ጎንደር የምርመራ ማዕከል ማቋቋምና የሕክምና መስጫ በመተማና አብርሃጅራ ሆስፒታሎች መስጠት ያስፈልጋል። ካልሆነ ታማሚዎችን በመኪና እስከ 200 ኪሎ ሜትር አጓጉዞ ጎንደር ማከም በመካከሉ ሌሎችን ለቫይረሱ ያጋልጣል ሲሉም ተናግረዋል።
በሽታው ሰዎችን ከሃይማኖታቸው ለመነጠል ሆን ተብሎ የመጣ አስመስለው ሕዝቡን የሚያሳስቱ አካላት በመኖራቸው ሕዝቡ ያለጥንቃቄ ወደሃይማኖት ተቋማት እየሄደ መሆኑንም ዶክተር ፋንታ ገልጸዋል። “እንዲህ ዓይነት ወሬዎች ሕዝቡን ሆን ብሎ ለማጋለጥ የሚነዙ መሆኑን ሕዝቡ መረዳት አለበት” ነው ያሉት ዶክተር ፋንታ።
በተለይም በምዕራብ ጎንደር በኩል ከሱዳን የሚገቡ ሰዎችን በተመለከተ ደግሞ በአግባቡ በማዕከላት ማቆየት እንደሚገባ ጠቅሰው ያሉት ማዕከላት ግን በቂ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል። ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ከመተማና ገንዳውኃ ለይቶ ማቆያዎች በተጨማሪ በድንኳን መጠለያዎችን ለማዘጋጀት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) እንደተናገሩት ደግሞ ግብረ ኃይሉ የኮሮና ቫይረስ ሁለንተናዊ ቀውስ እንዳያስከትል ጥረት እያደረገ የሚገኝ ቢሆንም በሚጠበቀው ልክ አበረታች ውጤቶች እየታዩ አለመሆኑን ገልጸዋል። በተለይ በምዕራብ ጎንደር ዞን ጠረፋማ ቦታዎች እየተስተዋለ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነም ነው ያስረዱት። እስካሁን በነበረው ሂደት የክልሉ መንግሥት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የማቆያ ቦታዎችን ለማስፋትም ሆነ አስፈላጊ ግብዓቶችን ሲያቀርብ የቆየ መሆኑን ዶክተር ሙሉነሽ ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ግን ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በተለይ በምዕራብ ጎንደር በየቀኑ ከ400 በላይ ሰዎች የሚገቡ መሆኑን ታሳቢ ያደረጉ የማቆያ ቦታዎች አለመኖር፣ የመመርመሪያና የሕክምና መስጫ ማዕከል በአቅራቢያው ባለመኖሩ በቅድመ መከላከሉ ሥራው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከመከላከል አንጻር የባሕሪ ለውጥ አለመምጣቱን የገለጹት ዶክተር ሙሉነሽ የግንዛቤ መፍጠሪያ መንገዱን መፈተሽ እንደሚገባም አመላክተዋል። “ሕዝቡ የምናስተምረውን እየሰማ አይደለም፤ ግን ማስተማሩን እንቀጥላለን። እስከመጨረሻው ማስተማርና መመርመር እንዲቀጥል እንጥራለን። የምርመራ ፕሮቶኮልም እንዲከለስ ተደርጓል” ብለዋል። የቤት ለቤት ቅኝትና የመስክ ጉብኝት እንደሚጠናከርም ዶክተር ሙሉነሽ አሳስበዋል።
ናሙና የሚሰበስቡ ባለሙያዎች የግል ደኅንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን ያስታወቁት ዶክተር ሙሉነሽ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
በተለይ በምዕራብ ጎንደር ከችግሩ ስፋት አንጻር ራሱን የቻለ የአደጋ ምላሽ ማዕከል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የፌዴራል መንግሥቱን ድጋፍ ጠይቀዋል። ተጨማሪ ስድስት የለይቶ ማቆያዎች እንደሚያስፈልጉትም ገልጸዋል። የሚገቡት ሰዎች ወደመላው ሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ለሀገር ኅልውና አስጊ መሆኑንም አመላክተዋል። በምሥራቅ አማራ በኩልም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች መሠል ትኩረት እንደሚሻም ተናግረዋል።
ከሃይማኖት አባቶች ቸልተኝነት ጋር በተያያዘም “ከሲኖዶሱና መጅሊሱ በላይ እናውቃለን እያሉ፣ ሕዝቡን ከሃይማኖትህ ሊነጥሉህ ነው እያሉ የሚያሳስቱ የሕዝብ ጠላት እንደሆኑ መንግሥት ያምናል” ብለዋል ዶክተር ሙሉነሽ።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገረመው ገብረጻድቅ ደግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና መመሪያዎችን የመተግበር ክፍተቶች መኖራቸውን አመላክተዋል። ሠርግና ክርስትና መደገስ፣ የንግድ ዕቃዎችን መደበቅ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ መፈጸም፣ ካራምቡላና ፑል ማጫወት፣ ኳስ መጫወት እየተስተዋሉ እንደሆነና ለወረርሽኙ እንደሚያጋልጥ አንስተዋል። በአስፈጻሚ አካላት በኩልም በአግባቡ አዋጅና መመሪያዎችን ያለማስከበር ችግር መኖሩን አቶ ገረመው ገልጸዋል። ከተገቢው በላይ ታሪፍ ማስከፈልና ሙሉ መጫን በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታይ ችግር እንደሆነም አስረድተዋል።
በገበያና ለቅሶ አካባቢዎችም አዋጅና መመሪያውን ያለማክበር እንደሚስተዋልም አቶ ገረመው አስረድተዋል። በተለይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተከለከሉ ጉዳዮችን ሰበብ እየፈለጉ በቃለ ጉባኤ እየፈቀዱ መሆናቸው ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
