
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለአማራ ክልል ሴት መሪዎች ከቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
ለአማራ ክልል ሴት መሪዎች ከቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ሥልጠና በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከ3R – 4 – CACE ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች ከምዕራብ አማራ ዞኖች የተውጣጡ 230 የሴት መሪዎች ናቸው።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ አሁን በክልሉ ያለው የተሻለ፣ የሰከነ እና የተረጋጋ ኹኔታ እንዲመጣ የሴት መሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ሴቶች ብልህ፣ አዋቂዎች እና ንጹህ ኾነው ሥራ በመሥራት እና ችግሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አንስተዋል፡፡
የሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለዚህ የሚያግዝ ሥልጠና ከወረዳ ጀምሮ ላሉ ሴት መሪዎች መሰጠቱ በጣም ጥሩ እና አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ከግጭት ማግስት ክልሉን እንዴት እንምራ፤ ሴቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የደረሰባቸውን የሥነ ልቦና ጫና ለመቀነስ ምን እንሥራ ለማለት ትልቅ እድል ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ስለኾነም ክልሉ ከሴት መሪዎች ብዙ ይጠብቃል ያሉት አቶ ይርጋ መሪዎች እድሉን ተጠቅመው የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት በመወጣት ለቀጣዩ ትውልድ ሸክም የምንቀንስለት መኾኑን አውቀን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
ክልላችን ከገጠመው ቀውስ ተምረን በቀጣይ ለማደግ እና ለመለወጥ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ይጠይቃልም ብለዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ሴቶች በግጭት ውስጥ ይበልጥ ተጎጅ፣ ይበልጡን ደግሞ የመፍትሔ አካል ናቸው ብለዋል፡፡ በግጭት የጤና እና የትምህርት ተቋማት ሲጎዱ የበለጠ ተጎጅ የሚኾኑት ሴቶች መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን በዚህ በግጭት ወቅት ሴቶችን የመፍትሔ አካል ማድረግ ከተቻለ የተረጋጋ፣ ሰላማዊ ሀገርና አካባቢ ለመፍጠር ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከግጭት በኋላ ባለው ጊዜ ሴቶችን በአግባቡ ተሳታፊ በማድረግ ለችግሮቻቸው ራሳቸው የመፍትሔ አካል እንዲኾኑ መሠራት እንዳለበት አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የሀገራችን ግማሽ የሚኾኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች ሲኾኑ በአመራር ሰጭነት እና በፖለቲካ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሴቶችን ተጠቃሚነት በክልላችን ለማረጋገጥ የሚሠሩ ሰፊ ሥራዎች ቢኖሩም በርካታ ችግሮችም አሉ ነው ያሉት፡፡
በክልላችን የተፈጠረው ግጭት በተለይም ሴት መሪዎች ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና የፈጠረ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በተከታታይ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየቱን አንስተው በራሳቸው የሚተማመኑ እና ችግሮችን የሚቋቋሙ ሴት መሪዎችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል፡፡
ስለኾነም ይህንን የሥነ-ልቦናዊ ጫና እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ለሴት መሪዎች የተዘጋጀው ከቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ሥልጠና መሰጠቱ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባለፉት ሁለት ዓመታት ቀውሱን ለመቀልበስ እና ልማትን ለማረጋገጥ መሠራቱን አንስተው፣ በስኬት የተከናወኑ የከተማዋን ፕሮጀክቶች እንዲጎበኙ ተሳታፊዎችን ጋብዘዋል፡፡
ሥልጠናው በቀጣይ ሁለት ቀናት ቀጥሎ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
