
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስከ 2042 ዓ.ም የሚዘልቅ የረጅም ዘመን ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ኅላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
የቢሮ ኅላፊው እንዳሉት የ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕድገት የዘላቂ ልማት ዕቅድ ከባለፉት ዓመታት ዕቅዶች በወሳኝ ነገሮች ይለያል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ካቋቋመች ጀምሮ የመካከለኛ ዘመን እንጅ የረጂም ዘመን ዕቅድ ታቅዶ እንደማያውቅ ዶክተር ደመቀ አስታውሰዋል፡፡
በመኾኑም በ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕድገት የዘላቂ ልማት ዕቅድ የረጅም ዘመን ዕቅድን ማካተቱ ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
የአጭር ጊዜ ዕቅድ የሚባለው የአንድ ዓመት ቆይታ ያለው ነው ያሉት ዶክተር ደመቀ ቦሩ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ እስከ አምስት ዓመት ይቆያልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የ10 ዓመት ዕቅድ የታቀደው በብልጽግና ዘመን መኾኑን ቢሮ ኅላፊው ተናግረዋል፡፡
የ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕድገት ዘላቂ የልማት ዕቅድ ከ2018 ዓ.ም እስከ 2042 ዓ.ም ከሚኖረው የጊዜ ቆይታ አንጻር ከአጭር እስከ ረጅም ዘመን የዕቅድ ዓይነቶች መሸፈኑ አንዱ መለያ ባሕሪው ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ዕቅዱ ልዩ ባሕሪው ሦስት አካላት ማለትም መሪዎች፣ ምሁራን እና ከፍተኛ ሙያተኞች ተባብረው እንዲሠሩ ማድረጉ ነው ብለዋል፡፡
መሪዎች የዕቅዱ ባለቤት መኾን አለባቸው ያሉት ዶክተር ደመቀ ዕቅዱ የንድፈ ሐሳብ እና የተለያዩ ሞዴሎች ችግር እንዳይገጥመው እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታዎችን የተረዳ እንዲኾን ምሁራንን ማሳተፍ አስፈልጓል ነው ያሉት፡፡
በፖሊሲ እና በስትራቴጂ የተተግባሪነት ችግር እንዳይገጥም ልምድ ያላቸውን ከፍተኛ ሙያተኞችን መጠቀምም ተችሏል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩት ዕቅዶች ጥቅል የኢኮኖሚ ማዕቀፍን በመያዝ ወደ ሴክተር የሚወርዱ እንደነበሩም አስረድተዋል፡፡ የ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕድገት ለዘላቂ ልማት ዕቅድ ግን ከጥቅል የኢኮኖሚ ማዕቀፍ እስከ ፕሮጀክት ድረስ የተናበበ ትስስር እንዲኖረው ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በዕቅዱ ክልሉ በስድስት የልማት ቀጣና መከፈሉንም ዶክተር ደመቀ ተናግረዋል፡፡
እነዚህም የጣና የልማት ኮሪደር፣ የደቡብ ምዕራብ አማራ፣ የሰሜን ምዕራብ፣ የተከዜ ኮሪደር፣ የማዕከላዊ አማራ እና የምሥራቅ አማራ እንደኾኑም ጠቅሰዋል፡፡
በዕቅዱ የ30 ዓመታት ዳታዎች በምሁራን እና ከፍተኛ ሙያተኞች ተተንትኖ መቅረቡን ያስታወሱት ቢሮ ኅላፊው ይህም ክልሉ ያለውን ጸጋ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ዕቅዱ የሕዝብ እንጅ የአንድ ዘመን ፓርቲ አይደለም ያሉት ዶክተር ደመቀ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡
በዋናነት ግን በተዋረድ ያሉ መሪዎች እና የመሪነት ሚና ያላቸው ሁሉ ዕቅዱ ተፈጻሚ እንዲኾን ሕዝብ ማንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ዕቅዱ ወደ ግብ ተቀይሮ መፈጸም ያለበት በተቋማት በመኾኑ ለተፈጻሚነቱ ሁሉም አካል በቅንነት በየደረጃው ያሉ መሪዎችን መደገፍ እና መተባበር ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡
የግጭት አዙሪት እና ድኅነት የክልሉ ችግሮች ኾነው በዕቅዱ ተለይተዋል ያሉት ዶክተር ደመቀ አሁን ይህ ዕቅድ ሁለቱንም ችግሮች እንዲፈታ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡
የዕቅዱ የመጨረሻ ግብም ዛሬ የዓለም ሀገራት ከደረሱበት ብልጽግና ለማድረስ፣ በቴክኖሎጅ ተወዳዳሪ ለመኾን፣ ደስተኛ ኅብረተሰብን ለመፍጠር ኾኖ ተቀምጧል ብለዋል፡፡
ከ2042 ዓ.ም በፊት ዕቅዱ በሦስት እርከን መቀመጡን ያስታወሱት ዶክተር ደመቀ የማገገም መርሐ ግብሩ እስከ 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
በ2022 ክልሉ ሰላማዊ ይኾናል ተብሎ ይታሰባልም ብለዋል። ”መዳረሻችን በቴክኖሎጂ ተስተካካይነት ብልጽግናን በማረጋገጥ እና ደስተኛ ኅብረተሰብን ማየት ነው” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን