ማኅበራዊ ተቋማትን ማውደም ለሕዝብ አለማሰብን የሚያረጋግጥ ነው።

15

ከሚሴ: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አርጡማ ፉርሲ ወረዳ ከፉርሲ ክላስተር ነዋሪዎች ጋር ምክክር ተካሂዷል።

በክላስተሩ ያሉ ቀበሌዎች በሸኔ ሲሰቃዩ የቆዩ ሲኾን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀት ቀጣናውን በመቆጣጠር ሰላም ማስፈን ችሏል።

የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና ከመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ጋርም ውይይት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የአርጡማ ክላስተር ነዋሪዎች የሸኔ ቡድን በቀበሌዎቹ በነበረበት ወቅት የትምህርት እና የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ ሕዝቡን ሲዘርፍ እንደነበር ገልጸዋል።

የቂጪጮ ቀበሌ ነዋሪ አህመድ ሀጂ ኡመር ለሕዝብ እታገላለሁ የሚል አካል ሕዝብ የሚገለገልበትን የውኃ ተቋም አያወድምም በማለት የሸኔ ቡድኑ በነበረበት ወቅት የውኃ ተቋሙን በማቃጠል ሕዝቡ የንፁህ መጠጥ ውኃ እንዳያገኝ ማድረጉን ተናግረዋል።

የጎልቦ አርባ ቀበሌ ነዋሪዋ ሶፊያ ኡስማን በበኩሏ ሸኔ በስፍራው በነበረበት ወቅት ልጆቻችንን ትምህርት ቤት እንዳንልክ ሲከለክለን እና ሰዎችን እያገተ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ሲቀበል ነበር ብለዋል።

ሕዝቡ የንፁህ መጠጥ ውኃ እንዳያገኝ የውኃ ተቋምን ያቃጠለውን አካል ሕዝቡ አንቅሮ ተፍቶት እየታገለው መኾኑን ጠቅሰዋል።

የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ኢብራሂም አሊ በቀጣናው በተሠራው የተቀናጀ የሕግ ማስከበር ሥራ ቀጣናው አኹን ላይ ሰላም መኾን ችሏል ብለዋል።

የጥፋት ኀይሉ ያወደመውን የውኃ ተቋም የወረዳው መንግሥት ከ600 ሺህ ብር በላይ በጀት በመመደብ ጠግኖ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራዊ ተቋማትን ማውደም ለሕዝብ ጥቅም አለማሰብን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የወረዳው ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመኾን ለሰላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው ሕዝብን ያሳተፈ የተቀናጀ የሕግ ማስከበር ተግባር ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለሴት መሪዎች ከቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
Next article”የ25 ዓመቱ ዕቅድ ለአማራ ክልል ዕድገትን እና ዘላቂ ልማትን ያጎናጽፋል” ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር)