በዓመቱ ከ325 ቶን በላይ የማር ምርት መመረቱን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

12

ጎንደር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎ወጣት ሀብታሙ ቸኮል በጎንደር ከተማ በንብ ማነብ ሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ተጠቃሚ ከኾኑ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።

‎በዘርፉ ከተሰማራ ከአራት ዓመታት በላይ እንደኾነው የተናገረው ወጣት ሀብታሙ በዓመት እስከ 200 ኪሎ ግራም ማር ያመርት እንደነበር ተናግሯል።‎በከተማ ግብርና የንብ ማነብ ዘርፍ በግል ከመሰማራት ይልቅ ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በጋራ መሥራት ቢችል የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው በመገንዘብ ሥራውን በጋራ እየሠራ መኾኑንም ተናግሯል።

ወጣት ሀብታሙ ቸኮል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮም ሀብታሙ ሰላም እና ጓደኞቹ በሚል ስያሜ በማኅበር ተደራጅተው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጿል። ቋሚ የሥራ ቦታ አለመኖር እና የማስፋፊያ ቦታ እጥረት መኖር ውጤታማ ለመኾን በሚያደርጉት ሂደት ላይ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መኾኑን ገልጿል።

‎ሌላው በሁለት የንብ ቀፎዎች ዘርፉን መቀላቀላቸውን ለአሚኮ የተናገሩት አቶ ዘመነ ሸጋው አሁን ላይ ከ60 በላይ ባሕላዊ፣ ዘመናዊ እና የሽግግር ቀፎዎች ባለቤት ኾነው ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል ። ‎በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ600 በላይ ኢንተርፕራይዞች በንብ ማነብ ሥራ ዘርፍ መሰማራታቸውን የከተማ አሥተዳደሩ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መላኩ ደምሌ ነግረውናል።


‎በበጀት ዓመቱም ከ325 ቶን በላይ የማር ምርት ተመርቷል ብለዋል። ‎ዘርፉን የተቀላቀሉ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ሙያዊ ድጋፍን ጨምሮ ኢንተርፕራይዞች የሚያነሷቸውን የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ‎የሌማት ቱሩፋት ውጥኑን እውን ለማድረግ በትጋት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመለው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን እንዲጎበኙ ጥሪ ቀረበ።
Next articleለሴት መሪዎች ከቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ሥልጠና እየተሰጠ ነው።