“የመንግሥትን መመሪያ በመቀበል ወደ መስኖ ሥራ በመግባቴ ዘመናዊ ኑሮ እየኖርኩ ነው፡፡” በመሥኖ የሚተዳደሩ አርሶ አደር

676

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአርሶ አደሩን የእርሻ ማሳ ውሎ ለመቃኘት በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራምቡቲ ቀበሌ ተገኝተናል፡፡ እረፍት አልባ የአርሶ አደሩ እጆችም ያለመታከት የመስኖ ሥራ ሲያከናውኑ ተመልክተናል፡፡

በምንጃር ወንዝ አካባቢ በሚገኙ የኢራምቡቲ ቀበሌ 46 አርሶ አደሮች በማኅበር በመደራጀት ወደ መስኖ ሥራ ገብተዋል፡፡ ለአርሶ አደሮች ወደ መስኖ ሥራ እንዲገቡ አስቀድሞ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በግብርና ዘርፍ የሚሠራው የግብርና ዕድገት ፕሮጀክት ከ800 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ከምንጃር ወንዝ ከ232 ሜትር ርቀት ላይ ሁለት የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች ተክሎላቸዋል፡፡ ጄኔሬተሮቹ በሴኮንድ 33 ሊትር ውኃ ይገፋሉ፤ በእነዚህ ጀነሬተሮች በመጠቀምም 33 ሄክታር የመስኖ እርሻ ያለማሉ፡፡

ወይዘሮ ሰርካለም ገዙ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራምቡቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ናቸው፡፡ በመስኖ እርሻ ማሳቸው ላይ ለሰባት ዓመታት ያለመታከት እየሠሩ በየዓመቱ የልፋታቸውን ውጤት እያገኙ ነው፡፡ በፊት የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን “የመንግሥትን መመሪያ በመቀበል ወደ መስኖ ሥራ በመግባቴ ዘመናዊ ኑሮ እየኖርኩ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተያዘው ዓመት እንኳን በአንደኛ ዙር የመስኖ እርሻ 69 ኩንታል ነጭ ሽንኩርት እና 52 ኩንታል ባሮ ሽንኩርት ማምረታቸውን ገልጸዋል፡፡ የተገኘውን ምርት ደግሞ ከ700 ሺህ ብር በላይ መሸጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ደረጃ እንዲደርሱ ድጋፍ እና ክትትል ያደረጉላቸውን የግብርና ልማት ባለሙያዎችም አመሥግነዋል፡፡

ፈገግታ የማይለያቸው ወይዘሮ ሰርካለም ወደ መስኖ ሥራ ከገቡ በኋላ በሠሩት ልክ ሀብት ማገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ እርሳቸው አካባቢ ያለውን ተሞክሮ በማስፋት ያለ በቂ አግልግሎት ከዓመት እስከ ዓመት የሚፈስሱ ወንዞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መሥራት እንዳለበት አስተያዬታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛውን አስተያዬት ሰጪ አርሶ አደር በመስኖ ሥራቸው ላይ አግኝተናቸዋል፤ አቶ ፀጋው ባሕሩ ይባላሉ፡፡ በቀበሌያቸው ከዚህ በፊት ለከብቶች ግጦሽ አግልግሎት ብቻ ሲውል የነበረውን መሬት ከወንዝ ውኃ በጄኔሬተር በመሳብ በመስኖ እያለሙ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ “ውኃ ሽቅብ ላይወጣ” የሚለው ተረት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራምቡቲ ቀበሌ እንደማይሠራም ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው የመስኖ እርሻ መጀመሩ በአርሶ አደሮች ዘንድ መልካም ፉክክር በመፍጠር ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲዳብር ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ የሥራ ሂደት የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ ብሩክ ወርቁ በወረዳው ከሚገኙ 27 ቀበሌዎች ውስጥ 13ቱ የመስኖ ውኃ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የከሰም እና የምንጃር ወንዞች በወረዳው አርሶ አደሮቹ በስፋት መስኖ እያለሙባቸው የሚገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከሁለቱ ወንዞች አግልግሎት የማያገኙ ቀሪ 14 ቀበሌዎችም የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ሥራ መሰማራታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተለይም በኮንክሪት ገንዳ ወይም ከጣራ ላይ ውኃ የማሰባስብ ዘዴ እና ‘ጂኦ-ሜምብሬን’ በመጠቀም አርሶ አደሮች በመስኖ ሥራ እንዲሰማሩ እየተበረታቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይትባርክ አብርሃም 2012ዓ.ም በጋ የምርት ዘመን በአንደኛ ዙር መስኖ እርሻ 191 ሺህ 339 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ በሁለተኛ ዙር የመስኖ እርሻ ደግሞ 368 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን የወረዳው አርሶ አደሮች በእርሻ ሥራ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤቱ መረጃ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ 3 ሺህ 930 አርሶ አደሮች በመስኖ እርሻ እየተሳተፉ ነው፡፡ በሁለቱም ዙር የመስኖ እርሻ ከ6 ሺህ 492 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለግብዓትነት ውሏል፡፡ አርሶ አደሮቹ ለውጤት ያበቃቸው ከግብርና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ሳይንሳዊ ምክር ተቀብለው ተግባራዊ ማድረጋቸው መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው- ከምንጃር ሸንኮራ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleለይቶ ማቆያ ከፀፀት ነፃ ያወጣው ኅሊና
Next articleወረርሽኙን ሰዎችን ከሃይማኖታቸው ለመነጠል የተፈጠረ አስመስሎ ሰውን ማዘናጋት ተገቢ አለመሆኑን ግብረ ኃይሉ አሳሰበ።