
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ከደቡብ ጎንደር እና ከሁሉም የጎጃም ዞኖች ከመጡ ወታደራዊ እና የሕዝብ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ሠራዊቱ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ባደረጉት የተቀናጀ ስምሪት ጽንፈኛው ቡድን ተመትቶ ቆሞ መዋጋት የማይችልበት ደረጃ መድረስ የቻለው መሪው ቀን ከሌት ተግቶ በመሥራቱ ነው ብለዋል።የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዡ አሁን ላይ ጠላት የሰው ኃይሉ እና የሎጀስቲክስ አቅሙ ተዳክሞበታል ነው ያሉት።
አንዳንድ አዋጊዎቹም ተመትተውበታል፤ ሌሎቹም እጅ ሰጥተዋል፤ ይህ ሊኾን የቻለው መሪው እያሰማራ እና ራሱም ጭምር እየተሠማራ በሰጠው አቅጣጫ በመኾኑ የሕዝብ ሰላም እስከሚረጋገጥ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።መሪው ቁልፍ ሥራውን በኀላፊነት መንፈስ በውጤት እየለካ ጠንክሮ መምራት ከቻለ የክልሉ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም እና ልማት የማይረጋገጥበት ምክንያት የለም ነው ያሉት።
ሌተና ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አሁን ላይ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሕዝባዊ እና መንግሥታዊ ድርጅቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን ኾኖ አስፈላጊውን ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ይህንን ለማስቀጠል የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ግዳጅ አስተማማኝ በኾነ መንገድ በመፈጸም በአጭር ጊዜ ክልሉን ወደተሟላ የልማት ማዕከልነት ማምጣት ይገባልም ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጄር ጄኔራል ግዛው ኡማ፣ የሁሉም ጎጃም እና የደቡብ ጎንደር ወታደራዊ እና የሕዝብ መሪዎች እንዲሁም የደብረ ማርቆስ እና የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
