ሀገራዊ ቅርሶች በሕግ ዐይን።

9

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቅርሶች የማንነት መገለጫዎች እና የታሪክ የመረጃ ምንጮች በመኾናቸው ለአንድ ሀገር እና ሕዝብ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

ከጠቀሜታዎቻቸው መካከል የምጣኔ ሃብት አቅምን ለማሳደግ፣ የፈጠራ ሥራን ለማጎልበት፣ ሀገራዊ ኩራትን ለመፍጠር፣ ማንነትን ለማወቅ፣ ለታሪክ መረጃነት፣ ለጥናት እና ምርምር፣ ለባሕል ልውውጥ እና ለገጽታ ግንባታ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ታዲያ እነዚህን ውድ የሀገር ሃብቶች መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት ሊኾን ይገባል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርሶች ጥበቃ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ስምምነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የ1972ቱ ባሕላዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶችን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ ስምምነት አንዱ ነው፡፡

ይህንን ስምምነት የፈረሙ ሀገራት ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን የመለየት፣ የመጠበቅ እና ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡ በሀገራችንም ቅርሶችን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 91(2) ላይ የሀገር የተፈጥሮ ሃብቶችን እና የታሪክ ቅርሶችን መጠበቅ የመንግሥት እና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ እንደኾነ ተቀምጧል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ አሁን በሥራ ላይ ያለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለቅርስ ጥናት እና አጠባበቅ አዋጅ ቁጥር 209/1992 ዓ.ም ወጥቷል፡፡

በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 3(9፣10 እና 11) ሀገራችን አሁን እየተጠቀመችበት ያለውን የቅርስ ትርጓሜ እና ተያያዥ ጉዳዮች አስቀምጧል፡፡ ቅርስ ማለት በቅድመ ታሪክ እና በታሪክ ዘመን የሰው ልጅ የፈጠራ እና የሥራ እንቅስቃሴ ውጤት የኾነ የተፈጥሮ የለውጥ ሂደትን የሚገልጽ እና የሚመሰክር በሳይንስ፣ በታሪክ፣ በባሕል፣ በሥነ-ጥበብ እና በዕደ-ጥበብ ይዘቱ ከፍተኛ ተፈላጊነት እና ዋጋ ያለው ማናቸውም ግዙፍነት ያለው እና ግዙፍነት የሌለው ነገር እንደኾነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ በቅርስ ጉዳይ ላይ ዋና ዋና የሚባሉ ተግባራትን በመተንተን የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራ በማን፣ በምን እና እንዴት መሥራት እንዳለበት ያመላክታል፡፡ ከእነዚህ ተግባራት መካከል የቅርስ ምዝገባ እና ጥገና ሥራዎች ይገኙበታል፡፡

ቅርስ ምዝገባ ማለት ቅርስን ለመለየት፣ ለመቆጣጠር፣ ለማጥናት፣ ለመንከባከብ፣ ለመጠገን፣ ለትምህርት እና ለመዝናኛነት አገልግሎት የሚውሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲቻል ስለ ቅርሱ ሰፊ መረጃ ለማሠባሠብ በተዘጋጀ ቅጽ መመዝገብ እና እንደ አመቺነቱ በፎቶግራፍ፣ በፊልም እና በቪዲዮ መቅረጽንም እንደሚጨምር በአዋጁ ተካትቷል።

ይህ ተግባር የቅርሶችን መረጃ በአግባቡ ለመያዝ እና ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ፤ ቅርሶችን ለጥናት እና ምርምር እንዲውሉ ከማድረግ ባለፈ ቅርሶች እንዳይዘረፉ ከጠፉም እንዲመለሱ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

የቅርስ ጥገናን በሚመለከት ጥገና ማለት ጥንታዊ ይዘቱ ሳይለወጥ ለቅርሶች የሚደረግ አጠቃላይ እንክብካቤ እና ጥበቃ መኾኑ ተደንግጓል። ይህም ቅርሶች መጠገን ያለባቸው ይዘታቸውን እንደጠበቁ በተሠሩበት ቁስ መኾን እንዳለበት ያመላክታል፡፡

የዚህ አዋጅ ዋና ዋና ዓላማዎች በአንቀጽ ቁጥር 4 ስር ተካትተዋል፡፡ እነሱም ቅርሶች በታሪክ ምስክርነታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ሳይንሳዊ ምዝገባ እና ቁጥጥር ማከናወን፣ ቅርሶችን ከሰው ሠራሽ እና ከተፈጥሮ አደጋዎች መከላከል ብሎም ከቅርሶች የሚገኙ ጥቅሞች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶች እገዛ እንዲያደርጉ ማስቻል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በዚህ አዋጅ ውስጥ በአንቀጽ 6 የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የተለያዩ ተግባር እና ኀላፊነቶች እንዳሉበት ተመላክቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቅርሶችን ለይቶ የመመዝገብ፣ የመንከባከብ እና የመቆጣጠር፣ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የማሠባሠብ፣ ጥናት እና ምርምር ማካሄድ እና ቅርሶች ከሀገር እንዳይወጡ የመቆጣጠር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ስለ ቅርስ ባለቤትነት በአንቀጽ 14/1/ ቅርሶች በመንግሥት ወይም በማንኛውም ሰው ባለቤትነት ሊያዙ እንደሚችሉ በአዋጁ ተካትቷል፡፡ በአንቀጽ 18 የቅርስ ባለይዞታ የኾነ ሰው ወይም ተቋም ስለሚጠበቅበት ግዴታዎች ተቀምጧል፡፡ ለአብነትም አንድ ሰው ወይም ተቋም በባለቤትነት የያዛቸውን ቅርሶች የመንከባከብ እና ስለቅርሱ አያያዝ እና አጠቃቀም የሚወጡ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የማክበር ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

በአንቀጽ 19 ስለ ቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ የተቀመጠ ሲኾን ጥገና ለማከናወን ቅድሚያ ከባለሥልጣኑ ወይም በተዋረድ ኀላፊነት ከተሰጠው አካል ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ አንቀጽ 24 ደግሞ ማንኛውም ሰው ቅርሶችን ለንግድ ዓላማ መግዛት እና መሸጥ እንደማይችል ያመላክታል፡፡

በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 29 ላይ ስለቅርሶች ፍለጋ ግኝት እና ጥናት ዋና ዋና ጉዳዮች የተቀመጡ ሲኾን ከእነዚህም መካከል ማንኛውም አካል ከባለሥልጣኑ የጽሑፍ ፈቃድ ሳያገኝ የቅርስ ፍለጋ፣ ግኝት እና ጥናት ማካሔድ እንደማይችል ተቀምጧል፡፡

እንግዲህ አዋጁ በቅርስ ጉዳይ የሚከናወኑ ተግባራት ማን ምን እንደሚሠራ የሚያትት እና የተከለከሉ ጉዳዮችንም ያስቀመጠ በመኾኑ ከዚህ አዋጅ በተቃራኒ ላሉ ወይም አዋጁን በሚጻረሩ ጉዳዮች የተቀመጡ ቅጣቶች አሉ፡፡ ይህም አንቀጽ 45 ሲኾን ስለቅጣት የተቀመጠበት አንቀጽ ነው፡፡

በዚህ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን ተላልፎ የተገኘ ሰው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከበድ ያለ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልኾነ በስተቀር ከስድስት ወር እስከ ሦስት ዓመት እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እንደ ጥፋቱ ክብደት እንደሚቀጣ ተቀምጧል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ማንኛውም ሰው በቅርስ ላይ የስርቆት ወንጀል ከፈፀመ ከሰባት ዓመት በማያንስ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ያትታል፡፡ እንዲሁም ማንኛውም ሰው ሆን ብሎ በቅርስ ላይ የማፍረስ ወይም ጉዳት የማድረስ ወንጀል ከፈፀመ ከ10 ዓመት በማያንስ ከ20 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ያስገነዝባል፡፡

ከላይ የተቀመጡት ቅጣቶች አንዳሉ ኾኖ በሥራ ኀላፊነታቸው አጋጣሚ ያገኘውን ቅርስ የሚያሰርቅ ወይም ጉዳት እንዲደርስ የሚያደርግ ከ15 ዓመት በማያንስ ከ20 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል በሚል በአዋጁ አስቀምጧል፡፡

በመረጃ ምንጭነት የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትን እና የቅርስ ጥናት እና አጠባበቅ አዋጅ ቁጥር 209/1992 ተጠቅመናል።

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይዎት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመሬትን የማበልጸግ አንዱ መንገድ!
Next articleየአፍሪካ ሀገራት ለኀይል አቅርቦት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል።