መሬትን የማበልጸግ አንዱ መንገድ!

10

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአኹኑ ወቅት ስለ ምርት እድገት ሲነሳ በጉልሁ ከሚነሱ ግብዓቶች መካከል አንዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) አንዱ ነው፡፡ አርሶ አደር አድማሱ መኮነን በምዕራብ ጎጃም ዞን በቡሬ ዙሪያ ወረዳ ይኖራሉ፡፡ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ሲኾን ከስድስት ዓመት በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) እየተጠቀሙም ነው፡፡

የኮምፖስትን ጠቀሜታ በእጅጉ የሚያደንቁት አርሶ አደር አድማሱ ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እያመረተ መኾኑን በኩራት ይናገራሉ፡፡ “ኮምፖስት ለእኛ ቀርቶ ለተተኪው ትውልድም ያገለግላል” ባይ ናቸው፡፡

በየዓመቱ ኮምፖስት እና ቨርሚ ኮምፖስት ያዘጋጃሉ፡፡ በሂደትም የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀሙን መቀነሳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ ጓሮአቸውን ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ነጻ በማድረግ ድንች እና በቆሎን በኮምፖስት ዘርተዋል፡፡

ነገር ግን የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከመጠቀም ሙሉ በሙሉ አልተላቀቁም፡፡ በቀጣይ ግን ለመሬቱ በሙሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለመጠቀም አቅደዋል፡፡ አንድ ጊዜ የጨመሩት ኮምፖስት እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ለማምረት እያስቻላቸው መኾኑን የጠቀሱት አርሶ አደር አድማሱ ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ዋጋው በጣም ከመጨመሩ ጋር በተያያዘም ኮምፖስት ዘላቂ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አጠቃ አይቸው ኮምፖስት በሦስት እንደሚከፈል እና እነርሱም መደበኛ፣ ቨርሚ እና ባዮ ሰለሪ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

አረንጓዴ ማዳበሪያ እና ባዮ ፈርትላይዘር የሚባሉም እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ኮምፖስት ያለው ጠቀሜታ ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ስለሚበልጥ አርሶ አደሩ እንዲጠቀመው እንደሚበረታታም አንስተዋል፡፡ ኮምፖስት የአፈር ምርታማነትን ሲጨምር የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ደግሞ የሰብልን ምርታማነት ይጨምራል፡፡

ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የአፈሩን ንጥረ ነገሮች ከልክ በላይ አሟጦ በመውሰድ ምርት የሚሰጥ ቢኾንም የአፈርን አሲዳማነት በመጨመር ይጎዳዋል፡፡ በአንጻሩ ኮምፖስት ግን ኦርጋኒክ በመኾኑ አፈሩን እስከ አራት ዓመት ድረስ ለም እና አምራች ያደርገዋል፡፡

ኮምፖስት በአካባቢ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የሚዘጋጅ፣ ኦርጋኒክ ነገሮችን የያዘ ለአፈር ምርታማነት ጠቀሜታ ያለው የማዳበሪያ ዓይነት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሀገር ውስጥ የማይመረተው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስለሚጠይቅ ጉዳቱ ከፍተኛ በመኾኑ ኮምፖስትን ተመራጭ እንደሚደርገው አቶ አጠቃ ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ኮምፖስትን አዘጋጅቶ የመጠቀም ልምድ እያደገ ቢኾንም ካለው ሰፊ ጠቀሜታ አኳያ በበቂ ደረጃ አለመለመዱን ገልጸዋል፡፡ በ2015/16 የምርት ዘመን ተፈጥሮ የነበረው የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እጥረትም ትምህርት ሊኾን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

አንድ አርሶ አደር በአማካይ 30 ሜትር ኪዩብ ኮምፖስት በማዘጋጀት ላይ መኾኑን የገለጹት አቶ አጠቃ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችም “የተሻሻለ ኮምፖስት”ን ለማዘጋጀት እና ለማስለመድ የሚተገብሯቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በ2017/18 የምርት ዘመን መንግሥት የደጎመውን 3 ሺህ 500 ብር ሳይጨምር የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ በአማካይ 8 ሺህ 500 ብር መኾኑን በማንሳት የዋጋውን ውድነት እና መጨመር አመላክተዋል፡፡ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በተከታታይ መጠቀምም መሬቱን ለአሲዳማነትም እንደሚያጋልጠው ተናግረዋል።

ኮምፖስትን በመጠቀም ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን የመተካት ሂደት ያሉበት መሰናክሎች ቀላል አለመኾናቸውን ባለሙያው አመላክተዋል፡፡ የትኩረት ማነስ፣ ከጥራት ይልቅ ቁጥር ላይ ማተኮር፣ በሪፖርት የሚገለጸው እና በተግባር የሚገኘው የተለያየ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

መሬትን ለመጭው ትውልድ ማቆየት የአኹኑ ትውልድ ኀላፊነት መኾኑን የገለጹ አቶ አጠቃ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን በአግባቡ በመተግበር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ሥራን ዘላቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልም ተጠያቂነት መኖር አለበት ብለዋል። “አፈር ላይ ሳይሠራ ስለ ግብርና ልማት እና የሰብል ምርት መጨመር ማሰብ አይቻልም” ነው ያሉት።

ለሥራዎች ዘላቂነት በተሰጠው የትኩረት ማነስ ምክንያት አርዓያ የነበሩ የአፈር እና የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ማዝለቅ አለመቻሉ ሌላኛው ማነቆ መኾኑን አንስተዋል። እንደ ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች ሁሉ ኮምፖስት ማዘጋጀትም የማበረታቻ ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባ ያነሱት አቶ አጠቃ አዘገጃጀት እና አጠቃቀሙን ተሞክሮ ማለዋወጥ እና ማስፋት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቀኝአዝማች መስፍን አርሶ አደሮች ስለ ኮምፖስት ጠቀሜታ በሚናገሩት ልክ በተግባር ላለመፈጸማቸው የስርጸት ሥራው በበቂ መጠን የተሠራ አለመኾኑን እንደ አንድ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡

በተግባር ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የተቀሰቀሰውን ያክል ለኮምፖስት አለመቀስቀሱ፣ የኮታ ዕቅድ እና የውሸት ሪፖርትም የችግሩ ምክንያቶች እንደኾኑ አንስተዋል፡፡ የተጠቀሱ ችግሮችን ቀርፎ መሥራት እንደተጠበቀ ኾኖ ጥራት ያለው ኮምፖስት አዘጋጅቶ መሸጥን ማስለመድ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ኮምፖስትን ለማዘጋጀት የሚጠይቀውን ጉልበት በመፍራት ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን ገዝቶ ‘በአቋራጭ መገላገልን’ የመምረጥ ስንፍናም እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡ ነገር ግን የቀጣዩ ትውልድ መሬትን የማደኽየት ልማድ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በቂ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አለ።
Next articleሀገራዊ ቅርሶች በሕግ ዐይን።