
ሰቆጣ: ሰኔ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017/18 የምርት ዘመን ከ120ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር በመሸፈን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ ገልጸዋል።
የታቀደውን ምርት ለማግኘትም ከቀበሌ እስከ ዞን ድረስ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የንቅናቄ መዶረኮች ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል። ዋግ ኽምራን በየዓመቱ ከሚያጋጥሙት ችግር ለማላቀቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የእርሻ ዘዴን እና ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን መጠቀም እንደሚገባ ነው የመምሪያ ኀላፊው ያብራሩት። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ 50 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የመደበ ሲኾን ከዚህም ውስጥ 32ሺህ ኩንታል በላይ ወደ ዞኑ መጋዝን መግባቱን አቶ አዲስ ተናግረዋል።
የከረመ 18ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ አኹን በዞኑ ይገኛልም ብለዋል። በአጠቃላይ በዋግ ኽምራ ከ50ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ መኖሩን ጠቁመዋል። ከዚህም ውስጥ ከ25ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለወረዳዎች የተከፋፈለ ሲኾን ወደ 16ሺህ ኩንታል የሚኾነው ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ነው ያሉት አቶ አዲሱ።
እንዳለፉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ አይደለም ያሉት የመምሪያ ኀላፊው አርሶ አደሮች በሰዓቱ የአፈር ማዳበሪያውን በመግዛት አገልግሎት ላይ እንዲያውሉ አሳስበዋል። በዋግ ኽምራ የክረምቱ ዝናብ ዘገይቶ ገብቶ ቀድሞ የሚወጣ በመኾኑ የተመረጡ ምርጥ ዘሮችን እና ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን