የነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑትን ሕጻናት በመደገፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

18

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ “የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ተኮር ተግባራትን እናከናውን” በሚል መሪ መልዕክት የአፍሪካ የሕጻናትን ቀን አክብሯል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የአፍሪካ የሕጻናት ቀን በአፍሪካ ለ35ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ መከበሩን ገልጸው በባሕር ዳር ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ቀበሌዎች ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል።

ቀኑ ሲከበር ሕጻናት መብቶቻቸው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆላቸው እንዲኖሩ የሚያስችሉ ሕጻናት ተኮር ተግባራትን ለማከናወን እንደኾነ ጠቁመዋል። በተለያየ ምክንያት በሕጻናት ማሳደጊያ የሚገኙ ሕጻናትን ብቁ የኾኑ ቤተሰብን በማዘጋጀት በአደራ እና በጉዲፈቻ እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ 220 የሚኾኑ ወላጅ አልባ ሕጻናት በተለያዩ የሕጻናት ማቆያዎች መኖራቸውን ገልጸው በዛሬው እለትም 12 ወላጅ አልባ ሕጻናትን በጉዲፈቻ ለአሳዳጊ ቤተሰብ ለመስጠት የተለዩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሕጻናት ለመታደግ የሕግ ከለላን መሠረት በማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለችግር ተጋላጭ የኾኑት ሕጻናት ጊዜያዊ እና ቋሚ የኾኑ ድጋፎችን በተከታታይ ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል።

መምሪያው የሕጻናት የትምህርት ተሳትፎን ለማጎልበት፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ መብታቸውን እንዲረጋገጥ ለማድረግ የሕጻናት ፓርላማን ጨምሮ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ መቆየቱን ነው ወይዘሮ ሰብለ የገለጹት።

ሕጻናት የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከትምህርት ተቋማት ጋር ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል። የሕጻናት ጉዳይ የሀገር ጉዳይ በመኾኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል የሕጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሕጻን ተምኪን ይሃ ሕጻናት አካባቢያቸውን፣ ታሪካዊ እና ጥንታዊ ሥፍራዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ ሀገራቸውን የሚያውቁ ኾነው እንዲያድጉ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግራለች።

በአሁኑ በቅት በርካታ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውንም ገልጻለች። ብቁ የኾነ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት እነዚህን ሕጻናት ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሡ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያለች።

በዝግጅቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በዓሉ ሲከበር በሕጻናት ደኅንነት ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ለመሥራት መኾኑን አንስተዋል።

ሕጻናትን ከጥቃት በመከላከል፣ ጥቃት አድራሾችን ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ እና የሕጻናትን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ሕገወጥ የሕጻናት ዝውውር እና የጉልበት ብዝበዛን ጨምሮ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የአጋር እና ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በሕጻናት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም መረባረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ቢሮው ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። ሕጻናት በተደራጀ ሁኔታ ድምፃቸው እንዲሰማ እና መብታቸው እንዲከበር በየደረጃው የሕጻናት ቀንን በማክበር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወነ መኾኑንም አብራርተዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑት ሕጻናት ሀገራቸውን እንዲወዱ፣ ለችግር የተጋለጡት ከችግራቸው ተላቀው ችግር ፈች ዜጎች እንዲኾኑ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዝግጅቱ በሕጻናት እንክብካቤ ዙሪያ መልካም ሥራ ያከናወኑ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። በሕጻናት የተሠሩ ልዩ ልዩ የፈጠራ ውጤቶችም ተጎብኝተዋል።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ25 ዓመታቱ የግብርና ልማት ዕቅድ እንዲሳካ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በቂ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አለ።