
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አሻጋሪ እና ዘላቂ ልማትን የሚያመጣ የ25 ዓመታት ዕቅድ ታቅዷል፡፡ ከ25 ዓመታት ዕቅዱ መካከል የግብርና ልማት ዕቅድ አንደኛው ነው፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የግብርና ልማት የ25 ዓመታት ዕቅድን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የ25 ዓመታቱ የግብርና ልማት ዕቅድ ከዚህ በፊት ከነበሩ ዕቅዶች በበርካታ ጉዳዮች ለየት ያለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት የግብርና ልማት ዕቅድ ሲታቀድ የገጠር ልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ከሚባለው ሀገር አቀፍ ፖሊስ ላይ ማዕከል ተደርጎ የሚሠራ ዕቅድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
እነዚህ ዕቅዶችም ትኩረታቸው በምግብ ሰብል ራስን መቻል እና ከተረጅነት መላቀቅ ላይ ያተኮረ የግብርና ልማት ስትራቴጂ ብቻ እንደነበራቸው አንስተዋል፡፡
ሌሎች ከግብርናው ዘርፍ ልናገኝ የሚገባውን ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል መልኩ የተቀረጹ አልነበሩም ነው ያሉት፡፡
በ25 ዓመታት የግብርና ልማት ዕቅድ ላይ ግን ግብርናው መዘመን አለበት፣ በአነስተኛ ማሳ ብቻ በሚያመርቱ አርሶ አደሮች ላይ ብቻ የተወሰነ መኾን የለበትም፤ ባለሁለት ፍኖት የግብርና ልማት አቅጣጫ መከተል አለብን ብለን ነው ያዘጋጀነው ብለዋል፡፡
ባለሁለት ፍኖት የግብርና ልማት አቅጣጫ ማለት አነስተኛ ማሳ ባላቸው አርሶ አደሮች ላይ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር ላይ ያተኮረ እና በእርሻ ኢንቨስትመንት ሰፋፊ የእርሻ ቦታ ወስደው በሚያመርቱ ባለሀብቶች ላይ ያተኮረ የግብርና ምርት እና ምርታመነት ማሳደግ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ግብርናውን ማሳደግ፣ ማዘመን፣ የሰው ኀይል ላይ ካተኮረው የግብርና ሥራ በመውጣት ወደ ሜካናይዜሽን መሸጋገርን ዓላማ ያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የ25 ዓመታቱ የግብርና ልማት ዕቅድ ለመስኖ ልማት ትኩረት እንደሰጠም አንስተዋል፡፡በአንድ ዓመት ያለውን የማምረት ጊዜ ከአንድ ጊዜ ወደ ሁለት እና ሦስት ጊዜ የማሸጋገር ብሎም መሬትን በላቀ ደረጃ የመጠቀም ስልትን የተከተለ ዕቅድ ነው ብለዋል፡፡
ዕቅዱ ስኬታማ እንዲኾን መላ ኅብረተሰቡ፣ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ምሁራን፣ ሙያተኞች እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በግብርና መኾኑን በመረዳት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን እንዲረባረቡ ይፈለጋል ነው ያሉት፡፡
የፋይናንስ አካታችነትን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ለመሥራት የፋይናንስ ተቋማትም ለዕቅዱ መሳካት ወሳኝ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዕቅዱ ከተሳካ በ25 ዓመታት መጨረሻ ላይ የኢኮኖሚ ለውጥ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ዘርፉ መበልጸግ ግብርናው ሁለት ሚና ይኖረዋል ያሉት ኀላፊው አንደኛው ለኢንዱስትሪ መስፋፋት መነሻ ኾኖ ያገለግላል፣ ሁለተኛው ደግሞ ኢንዱስትሪውን በመመገብ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
በዕቅዱ ላይ በተቀመጡ እሳቤዎች ላይ ተመሥርቶ መጓዝ ከተቻለ ግብርናው ለኢኮኖሚ የሚያበርከተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
