ለይቶ ማቆያ ከፀፀት ነፃ ያወጣው ኅሊና

202

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከሀገር ሸሽተው፣ ባሕር አቋርጠው የተሻለ ሕይወት ለመምራት ወስነው መዳረሻቸውን ሶማሌ ላንድ አድርገው ከነበር ሰነባብተዋል፡፡ ወደ የመን ለመግባት አመች ሁኔታ ይፈጠራል በሚል በሶማሌ ላንድ ቦሳሶ ወደብ አቅራቢያ ለሁለት ወራት ያክል መሽገውም ነበር፡፡ ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም አዲሱ ክስተት መሆኑን ተከትሎ ይገቡበት ቤት፣ ይጠጉበት ጎረቤት ቢያጡ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ “ማን እንደ ሀገር?” ብለውም በጅግጅጋ በኩል የትውልድ ቀያቸው ደርሰዋል፤ የቆቦ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው አቶ አማረ በላይ፡፡

የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አማረ “የኮሮና ቫይረስ ሊኖርብኝ ይችላል” የሚል ስጋት ነበራቸው፤ እርሳቸውን ጨምሮ ወደ ለይቶ ማቆያ ለመግባት ፍላጎት ከነበራቸው 20 ገደማ ተጓዦች ጋር በመመካከርም ወደ ወልዲያ ከተማ ከመግባታቸው በፊት ለይቶ ማቆያ መግባት እንደሚፈልጉ ለመንግሥት አካላት ቀድመው አሳወቁ፡፡ ወደ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ ተወስደውም ከ14 ቀናት ቆይታ በኋላ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ያለ ምንም ስጋት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለውም ቤተሰባዊ ፍቅራቸውን ማጣጣም ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ “ተመርምሬ ከቫይረሱ ነፃ መሆኔን በማረጋገጤ የተለየ ስሜት ተሰምቶኛል፤ ይህን በማድረጌ ከፀፀትና ከኅሊና ክስ ነፃ ሆኛለሁ” በማለት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አጫውተውናል፡፡

ማንኛውም አጠራጣሪ ሁኔታ ሲገጥም እራስን ለይቶ ማቆየት የተሻለ መፍትሔ እንደሆነም መክረዋል፡፡ ሰዎች ቫይረሱ ቢኖርባቸውም እንኳን እንደሚድኑ ውስጣቸውን ማሳመን፣ በሽታውን ለቤተሰቦቻቸው ላለማስረከብ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ነገር ግን ይህ እየሆነ አለመሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ አብረዋቸው ከሶማሌ ላንድ የተመለሱ እንደመጡ ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ግለሰቦች እንደነበሩም መስማታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ወረርሽኙ አሳሳቢ መሆኑ እየታወቀ ወደ ማቆያ ከገቡ በኋላ መዳረሻቸውን የሚያጠፉ ግለሰቦች እየተበራከቱ መሆኑንም አብመድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ በተነገረባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት በምዕራብ ጎንደር ዞን የለይቶ ማቆያ ገብተው የነበሩ 37 ግለሰቦች ተሰውረዋል፡፡ ከእነርሱ ውጭም በማቆያ ቦታዎቹ ገብተው መጥፋታቸው የተረጋገጡና የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ማኅበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ አሳውቀዋል፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለፃ የተጠናከረ የለይቶ ማቆያና በማቆያዎቹ ውስጥ የተሟላ የመገልገያ ቁሳቁስ አለመኖር ግለሰቦቹ ከማቆያዎቹ እንዲሸሹ እያደረጉ ያሉ ገፊ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ በለይቶ ማቆያዎች እየተስተዋሉ ያሉ የቁሳቁስ፣ የምግብና መሰል እጥረቶችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አሳውቋል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዋለ በላይነህ እንደተናገሩት ጉድለቶችን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ የለይቶ ማቆያዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችን በማስተባበር መሟላት ያለባቸውን ምግብና ቁሳቁስ ለማሟላትም እየተሠራ ነው፡፡ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ አካባቢዎች ቢሮው ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በለይቶ ማቆያ በሰዎች የጤና ሁኔታ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ቀውስ ለመቀነስ የሚያስችል በመሆኑም ልምዱ መዳበር እንዳለበት አቶ ዋለ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በተለይ በምዕራብ ጎንደር ጠረፋማ አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ስለሚችል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፌዴራል መንግሥትን ድጋፍ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል።
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበጋምቤላ በቀን 180 ናሙናዎችን መመርመር የሚያስችል የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማሽን ሥራ ጀመረ።
Next article“የመንግሥትን መመሪያ በመቀበል ወደ መስኖ ሥራ በመግባቴ ዘመናዊ ኑሮ እየኖርኩ ነው፡፡” በመሥኖ የሚተዳደሩ አርሶ አደር