
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎችም መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተዋል።
የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች ባሕር ዳር ከተማ ሲደርሱ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የከተማዋ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎችም ነዋሪዎች ተቀብለዋቸዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ትላንትና አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያስገነባቸውን ፕሮጀክቶች ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እየሠራ መኾኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል። የጎንደር የኮሪደር ልማት ሥራ ያለፈውን ታሪክ ከአሁኑ እና ከወደፊቱ ትውልድ ጋር አስተሳስሮ እየተገነባ ስለመኾኑም በጎንደር ቆይታቸው ማመልከታቸውን አንስተዋል።
በመቀጠልም ወደ ጣና ሐይቅ ዳርቻ ተጉዘው ጎርጎራ እና አካባቢውን መመልከታቸውን ገልጸዋል። ጎርጎራ ላይ የተሠራው ሪዞርት የሰው ልጅ አስተውሎት፣ መጠበብ እና አርቆ ማሰብ ሊፈጥረው የሚችለውን ትጋት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በጎርጎራ አምሳል የሚገነባው ጣና ማሪናም ከጎርጎራ ጋር ተደማምሮ ጣና ሐይቅን “የምድር ገነት” የሚያሰኝ ድንቅ ሥራ ነው ብለዋል።
“ጎርጎራ ኢትዮጽያውያን ከፍ ያለ ነገር የምንወድ እና መሥራት የምንችልም እንደኾንን የሚያመላክት ነው” ሲሉም ገልጸዋል። ጎርጎራ የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍ የሚያደርግ ሥለመኾኑም ተናግረዋል።
ዛሬ ወደ ባሕር ዳር ሲገቡም የከተማው ሕዝብ ያደረገላቸው አቀባበል እውነትም ባሕር ዳር የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የደግነት፣ የእንግዳ ወዳድነት እና ተቀባይነት ማዕከል እንደኾነች ያሳየ ነው ብለዋል። ለተደረገላቸው ቤተሰባዊ አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ የባሕር ዳር ከተማን የኮሪደር ልማት ሥራ፣ አዲሱን የዓባይ ድልድይ፣ የጣና ዳርቻ አረንጓዴ ልማቶችን፣ የባሕር ዳርን ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና ሌሎችንም የልማት ሥራዎች ተመልክተዋል።
“የባሕር ዳር ኮሪደር ልማት አልቆ ማሰብ ከተቻለ ባሕር ዳርን የበለጠ ውብ እና የአፍሪካ ምርጧ ከተማ ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ሥራ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። መንገዶቹ ሰፍተዋል፣ ተውበዋል፤ ጣና ውበቱ ተገልጦ ለሕዝቡ ዕይታ ምቹ እና ማራኪ ኾኗል ብለዋል።
ባሕር ዳር እና አካባቢው ተፈጥሮ ውበት የቸረው ነው፤ ሐይቁ፣ አረንጓዴ ዛፎች፣ ኮረብታዎች እና ታላቁ የዓባይ ወንዝ ተሰናስለው የወለዱት ድንቅ ውበት አለ ብለዋል።
ይህ ውበት የሰው ልጅ እጆች፣ ጥበብ እና አስተውሎት ሲጨመርበት ደግሞ ምን ሊመስል እንደሚችል የኮሪደር ልማት ሥራው አሳይቶናል ብለዋል። አሁንም ቢኾን ተጨማሪ ሥራዎችን በማከናወን ተፈጥሮ የቸረችውን ውበት የበለጠ ማላቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“የልማት መሥኮት ተደጋግሞ ላይከፈት ይችላል፤ ለባሕር ዳር ከተማ የልማት መሥኮት ተከፍቶላታል፤ ይህንን እድል ተጠቅሞ ልማትን ማሳለጥ ይገባል” ሲሉም መክረዋል።
ልማቶች ሁሉ መሠረታቸው ማኅበረሰብ ነው፤ የባሕር ዳር አካባቢ ማኅበረሰብ ደግሞ የማደግ እና የመለወጥ ፍላጎት ያለው ሕዝብ ነው፤ በአልባሌ ነገር ሳይወሰድ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ላይ በብርታት መሳተፍ እና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም በጣም ትልቅ ሥራ ነው፤ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማካሄድም በሚያስችል መልኩ እየተገነባ ነው ብለዋል።
ይኹን እንጂ ሥራውን በፍጥነት ማጠናቀቅ እና ለውድድር ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በቀጣይ አሕጉራዊ ጨዋታዎችን በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለማዘጋጀት እየታሰበ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የእድገት ቁልፉ ልማት ነው፤ የልማት ደግሞ መደላድሉ ዕውቀት እና አስተውሎት ነው፤ የአማራ ክልል ሕዝብ ለሥራ ብርቱ እና እድገትን ውርሱ ለማድረግ የሚተጋ ሕዝብ ነው ብለዋል።
ይህንን የቆየ ትልቅ እሴት ለመሸርሸር የሚጀማመሩ ነገሮች አልባሌ እንደኾኑም ጠቅሰዋል።
በመኾኑም በአርቆ አስተዋይነት መቆም እና ሕዝብን እና ሀገርን በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ብቻ ጊዜን ማሳለፍ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
