ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሥራ ነው።

16

ደብረማርቆስ፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ተኮር ተግባራትን እናከናውን” በሚል መሪ መልዕክት የአፍሪካ ሕጻናት ቀን በአፍሪካ ለ35ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተከብሯል።

 

የሕጻናት ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ ቤተሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ጥበቃ፣ መብት እና ደኅንነታቸውን ለማስከበር በሚል በየዓመቱ ሰኔ 9 ቀን የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ተከብሮ ይውላል።

 

የዚህ ዓመት የአፍሪካ ሕጻናት ቀንም በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መሪ መልዕክቱን መሠረት ተደርጎ ነው በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረው።

 

በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሕጻናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ እህትነሽ ጌቴ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።

 

ከትምህርት ገበታ ውጭ ያሉ ሕጻናትን በቀጣይ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠሩ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል።

 

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ ግንኙነት እና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አበባው ግዛቸው የሕጻናትን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሕጻናት ምቹ የኾነ አካባቢ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።

 

አሁን ላይ የተከሰተው የሰላም እጦት ሕጻናትን ለሥነ ልቦና ችግር እየዳረገ ይገኛል ያሉት አቶ አበባው ሕጻናትን ካለባቸው የተለያዩ ችግሮች እንዲወጡ ሕጻናት ተኮር ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

 

በመድረኩ የተገኙ ሕጻናትም የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች እንደመኾናቸው መብት እና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ከማድረግ ባሻገር ተቋማት ልጆች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

 

የአፍሪካ ሕጻናት ቀን በአፍሪካ ለ35ኛጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሲከበር ሕጻናት የፈጠራ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጎንደር ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ያስተሣሠረች እና ሕልም በተግባር የተገለጠባት ከተማ መኾኗን የጥበብ ባለሙያዎች ተናገሩ።
Next article“የልማት መደላድሉ ዕውቀት እና አስተውሎት ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ