
ጎንደር፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተወጣጡ የጥበብ ባለሙያዎች ጎንደር እና አካባቢውን እየጎበኙ ነው።
የጥበብ ባለሙያዎች ቀደምት አባቶች ሠርተው ያለፉትን የኪነ ሕንፃ ጥበብ ታሪክ እና በአሁኑ ትውልድ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን ተመልክተዋል።
ለአብነት የመገጭ ፕሮጀክት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ዕድሳት እና የጎንደርን የኮሪደር ልማት ጎብኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ባሕል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኀላፊ እና የቡድኑ አስተባባሪ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሔር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጋር ከተወያዩ በኃላ በአራቱ ማዕዘን ሀገራቸውን የበለጠ ለማወቅ እየጎበኙ ይገኛሉ ብለዋል።
አንዱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቡድን ጎንደር እና አካበቢውን እየጎበኘ መኾኑን ገልጸዋል። የጎንደር ሕዝብም ደማቅ አቀባበል እንዳደረገላቸው ጠቅሰዋል።
የሚሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ኪነ ጥበቡን እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ታሣቢ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
ይህ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይኾን በክልሎችም እየተተገበረ እንደኾነ አንስተዋል።
ለአብነትም የጎንደር አብያተ መንግሥታት ዕድሳት እና የመስቀል አደባባይ የማስዋብ ሥራ ለጥበብ ሥራዎች ብዙ ማሠራት የሚችሉ እንደኾኑ አብራርተዋል።
ፀሐፍት፣ የትያትር ባለሙያ፣ የፊልም እና የሙዚቃ ባለሙያዎች በሀገራቸው እየተገለጡ ያሉ ታሪካዊ እና የመስዕብ ቦታዎችን በመጠቀም ሥራዎቻቸውን መከወን እና ለሌሎች ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።
ለዚህም ነው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ታሪካቸውን እና ተፈጥሮ የቸረውን ከባቢ እንዲመለከቱ እየተደረገ ያለው ተብሏል።
ጎንደርን ከአስር ዓመታት በኀላ ለሁለተኛ ጊዜ እየተመለከቱ ያሉት ድምፃዊ ምትኩ በቀለ የጎንደር አሁናዊ ለውጥ ተስፋን ያላብሳል ብለዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ዕድሳት መከናወኑ ለቀጣይ ትውልድ ታሪክን ለማስተላለፍ ህያው ምስክር እንደኾነም ተናግረዋል።
ኪነ ጥበብን ተጠቅመን ሀገርን ለመገንባት የበኩላችንን መወጣት ሙያዊም ኾነ ሀገራዊ ኀላፊነት ነው ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የኪነ ጥበብ አስተዋዋቂ ምህረት ምትኩ በዝና የማውቃትን ጎንደር ከተማን በአካል በማየቴ ታሪክን እና የኪነ ሕንፃ የከፍታ ዘመንን እንድረዳ አድርጎኛል ነው ያሉት።
አባቶቻችን የሠሩትን ታሪክ ለማስቀጠል ይህ ትውልድ በዕድሳቱ የራሱን አሻራ እያስቀመጠ እና ለጎንደር የሚበጀ አዲስ ታሪክ እየተሠራ እንደኾነም ተረድቻለሁ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ማሣያ የኾነችው ጎንደር ዳግም እየተሞሸረች እንደኾነም መረዳታቸውን ጠቅሰዋል።
አርቲስት ሳሊያ ሳሚ በበኩላቸው ጎንደርን ለመጀመሪያ ጊዜ መጎብኘታቸውን አንስተዋል። ቀደምት ድንቅ ኪነ ሕንፃዎችን መመልከቴ አስደንቆኛል ብለዋል።
አንዳንድ ሀገራት ሀገር ኾነው ባልቆሙበት ጊዜ ኢትዮጵያ አስገራሚ ሥራዎችን ማከናወን የቻለች ሀገር እንደነበረች አውቀን በጋራ ለከፍታዋ ልንበረታ ይገባል ነው ያሉት።
አንዳችን የሌላውን አካባቢ እያወቅን ሙሉ ኢትዮጵያን ስንረዳ ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ ይረዳናል ያሉት አርቲስቷ ጥበብን ለሀገር ግንባታ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል።
የጥበብ ባለሙያዎቹ ጎንደር ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ያስተሣሠረች እና ሕልም በተግባር የተገለጠባት ከተማ ናትም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
