በሥነ ምግባር የተቃኘ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ሕጻናት ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

22

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ሕጻናት ቀን በአፍሪካ ለ35ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ ” የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ተኮር ተግባራትን እናከናውን” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ተወካይ እና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጋዜጠኛ መሠረት አስማረ አሚኮ የሕጻናትን እና አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በሁሉም የሥርጭት አማራጮች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በተሠራው ሥራም ማኅበረሰቡ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሠጠው እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት።

በቀጣይም ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አሚኮ ጥልቀት ያላቸው ዘገባዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ነው ያብራሩት።

የሕጻናትን መልካም ግብረ ገብነት ከሚቀርጹ ተቋማት መካከል ሚዲያ አንዱ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የልጆችን አስተዳደግ የሚወስኑ መልካም እሴቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲያድግ ሚዲያውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበትም መክረዋል።

የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ አካል ጉዳተኞች ለዘመናት በሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተገልለው መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተቋማት የእቅዳቸው አካል አድርገው እንዲሠሩ ፌዴሬሽኑ እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

የአካል ጉዳተኞች ድምጽ በመኾን ከሚሠሩ ተቋማት ውስጥ ደግሞ አሚኮ ቀዳሚ መኾኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ አካል ጉዳተኞች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካዊ ዘርፍ እንዲካተቱ ተቋማት በዕቅዳቸው አካትተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አሻግሬ ዘውዴ በክልሉ በተፈጥሮም ኾነ በሰው ሠራሽ ቸግሮች ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ እና በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ቁጥር መበራከቱን ገልጸዋል።

ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ባለፉት ወራት ሕጻናት አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ መስህብ ቦታዎችን፣ የሕጻናት መዝናኛ ቦታዎችን፤ የሕጻናት ማሳደጊ ተቋማትን እንዲጎበኙ እና እንዲያውቁ መደረጉን ነው የገለጹት።

ልዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በኢግዚቢሽን እንዲያቀርቡ፣ የሕፃናት ፓርላማዎችን እና የሕጻናት መብቶች እና ጥበቃ ኮሚቴዎችን የማጠናከር ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።

መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ አጋር አካላትን እና ማኅበረሰቡን በማስተባበር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሕጻናት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ሃብት የማሠባሠብ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

ከ1ሚሊዮን 298 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ በአማራጭ የሕጻናት ድጋፍ እና ክብካቤ አገልግሎቶች ላይ ግንዛቤ መፈጠሩን ነው የተናገሩት።

ለችግር የተጋለጡ ሕጻናት ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ ተላቅቀው ለሀገራቸው ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ሁሉም ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የለውጥ ሥራዎች ተመለከቱ።