አረንጓዴ ልማት በኢትዮጵያ

26
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሥራ ዋና የኢኮኖሚ ምንጫቸው ለኾኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ብዙ ተፈትነዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ዳፋ በየወቅቱ ድርቅ እንዲጎበኛት ምክንያት ኾኗል፡፡ ይህን ለመከላከል አረንጓዴ ልማትን ማጠናከር ሁነኛ መድኃኒት ነው፡፡ ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ካለው ቀውስ መዳኛ መንገዱ የአረንጓዴ ልማት ነው በሚል ወደ ሥራ ከገባች ቆየት ብላለች፡፡
የአረንጋዴ ልማት ሥራ በልዩ ትኩረት መሠራት የተጀመረው በ2011ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አማካኝነት ነበር።
በመጀመሪያው ምዕራፍም በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ዓላማን በማንገብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዕቅድ በላይ ከ25 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የእጽዋት ችግኞችን መተከልም ተችሏል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ”ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፈው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት መረጃ ያሳያል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አንድ ሀገር ብቻ ተረባርቦ አካባቢውን አረንጋዴ በማድረግ የሚመለስ እንዳልኾነ የተረዳችው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የአፍሪካ ሀገራትን ለማሳተፍ ከፍተኛ ርብርብ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
በአካባቢ መራቆት ሳቢያ ዓለምን እየፈተናት የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥም ሊድንና ሊታከም የሚችለው በተፈጥሯዊ መንገድ በሚከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ የልማት ሥራዎች እንደኾነ አፍሪካውያን አምነው በተቋማቸው አማካኝነት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡
ሁሉም በአንድ ልብ ኾኖ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንዲቻል የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ACS) በ2023 በናይሮቢ ኬንያ ተካሂዷል። ጉባኤው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከአስተናጋጇ ኬንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነበር።
ጉባኤው በዋናነት በአረንጓዴ እድገት እና በአየር ንብረት ፋይናንስ መፍትሔዎች ላይ የአፍሪካ መሪዎች ለአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት እና ደጋፊ አጋሮች የተግባር ጥሪ በማቅረብም ስኬታማ ሥራ ሠርቷል።
በተለይም ይህ መድረክ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ለ ግሩፕ ሃያ (G20) ሀገራት፣ ለዓለም ባንክ፣ ለዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባዎች እና ሌሎች ተቋማት ለማስገንዘብ እንደ መስፈንጠሪያ ኾኖ አገልግሏል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝር እቅዶችን እንዲያዘጋጁ፣ ኢንቨስትመንቶችን እንዲቀርጹ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻያዎችን እንዲገፉ ትልቅ እገዛም አድርጓል።
በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ልማት ጉዳዮች ላይ የአፍሪካን የተባበረ ድምፅ ማጠናከር፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት የአየር ንብረት ለውጥ እና የሚቋቋም ልማት ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሐ ግብር ያሉ አህጉራዊ መርሐ ግብሮችን ለመተግበር ድጋፍ ማሠባሠብ ላይም የራሱን አሻራም ማሳረፍ ችሏል።
ይህ ጉባኤ ሁለተኛውን መድረክ በኢትዮጵያ ይካሄዳል። ባለፈው ጉባኤ ላይ የተመከረባቸው ጉዳዮች ምን ያክል ተግባር ላይ እንደዋሉ በመገምገም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራል።
ይህ ጉባኤ ለኢትዮጵያውያን ጥሩ አጋጣሚ ነው። በተለይም ሀገሪቱ ችግሩን ለመቅረፍ የሄደችበትን ርቀት የምታሳይበት እና ለአረንጋዴ ልማት ሥራ ሁሉም ትኩረት እንዲሰጡ ተሞክሮዎቿን የምታጋራበት እንደሚኾንም ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ላይ የማይናወጥ አቋም እንዳላት ባለፉት ዓመታት አሳይታለች። ይህንንም በሀገር ውስጥ ከመሥራት ባለፈ ጎረቤት ሀገራትን መሠረት አድርጋ የአረንጓዴ ልማት ሥራንም በስፋት መሥራት ችላለች፡፡ በመረጃ ምንጭነት የአፍሪካ ኅብረት እና የኢትዮጵያ ደን ልማትን መረጃዎች ተጠቅመናል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ
Next articleጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።