በጋምቤላ በቀን 180 ናሙናዎችን መመርመር የሚያስችል የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማሽን ሥራ ጀመረ።

158

በጋምቤላ ክልል ሥራ የጀመረው የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማሽን በቀን እስከ 180 ናሙናዎችን የመመርመር አቅም እንዳለው ተጠቅሷል። ምርመራው ከተጀመረ ወዲህ ሰባት ናሙናዎች ተመርምረው ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡


የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት በሀገሪቱ የኮሮኔ ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወቀ ጀምሮ በጋምቤላ ክልል በርካታ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡

ክልሉ በርካታ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙና ከደቡብ ሱዳን ጋርም በሰፊው የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮሮናቫይረስን ለመመርመር የሚያስችል ማሽን ሥራ እንዲጀምር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየተቱንም አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው በተለያዩ ቦታዎች በሚደረገው ሙቀት ልየታ ኅብረተሰቡ ያለምንም ፍራቻ ምርመራ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ካን ጋትሉዋክ ደግሞ የክልሉ መንግሥት ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር በክልሉ ቀደም ሲል ለኤች አይ ቪ መመርመሪያ ያገለግል የነበረው ማሽን አዲስ ሶፍት ዌር በመጫን ለኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲውል መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ውጤቶችን ሲገልፁ እንደነበር ጠቅሰው በክልሉ ምርመራ መጀመሩ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ በተጨማሪ በክልሉ በተለያዩ ለይቶ ማቆያዎች ለሚገኙ ዜጎች በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም አቶ ካን ተናግረዋል፡፡

ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመመርመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በክልሉ ከሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት የተገኝው መረጃ ያመልክታል፡፡

Previous articleበቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የሚገነቡት ትምህርት ቤቶች ለ2013 የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንደሚሆኑ ጽሕፈት ቤቱ አስታወቀ፡፡
Next articleለይቶ ማቆያ ከፀፀት ነፃ ያወጣው ኅሊና