ዕውቀትን፣ ቴክኖሎጂን እና ክህሎትን መሠረት ያደረጉ ማሻሻያዎች በማከናወን የአገልግሎት አሰጣጡን ማሳለጥ ይገባል።

10
ፍኖተሰላም፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ አሥዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግ አረገ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም ዕውቀትን፣ ቴክኖሎጂን እና ክህሎትን መሠረት ያደረጉ ማሻሻዎች ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የማኅበረሰቡን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሲቪል ሰርቫንቱ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እና የማኅበረሰቡን አገልግሎት እርካታ ለመጨመር በየጊዜው የሠራተኞችን የአገልግሎት አሰጣጥ መፈተሽ ይገባልም ነው ያሉት።
የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙላት ቸኮል ሪፎርሙ ሠራተኞች በአመለካከት እና በአቅማቸው ተለክተው እንዲያገለግሉ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
አሠራሮችን ዲጂታላይዝድ ማድረግ በተገልጋዩ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመከላከል እንደሚያግዝም አንስተዋል። የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንግሥቱ ተስፋዬ በከተማ አሥተዳደሩ እስካሁን ከከተማ ቦታ ጋር በተያያዘ በቂ የተደራጀ መረጃ ባለመኖሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ከከተማ አገልግሎት ጋር በተገናኘ በየጊዜው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመተባበር ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ ቅሬታ እና አቤቱታ አሥተዳደራዊ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጎጃም አበረ ከማኅበረሰቡ የሚመጡ አቤቱታዎች እና ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙ እና ተገልጋዩ በአገልግሎት አሰጣጡ እንዲረካ እየተሠራ መኾን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየፌዴራል መንግሥት እና የክልል ከፍተኛ መሪዎች የባሕር ዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ ነው።
Next article“ባሕር ዳር ተፈጥሮ እና የሰው ጥበብ ሲሠናኙ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እያሳየች ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ