
ደብረማርቆስ፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ የመንግሥት አገልግሎት አሥተዳደር እና ሪፎርምን ለማስተዋወቅ በዞን እና በወረዳ ከሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ የሥራ ኀላፊዎች ለጠንካራ ሀገር ግንባታ የመንግሥት ሠራተኛው ድርሻ ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። ጠንካራ መሪ እና ጠንካራ ሠራተኛ ጠንካራ ተቋም ይፈጥራል ያሉት ተሳታፊዎች በፊት በነበሩ መመሪያዎች የሚነሱ ጉድለቶችን በሪፎርሙ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ የሠራተኛውን የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ ተገቢ እንደኾነ ገልጸዋል።
ወቅቱን እና ሀገራዊ ኹኔታዎችን ያገናዘበ ዘመናዊ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን በማጥራት መዋቅሮችን ወደ ታች ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሸጋው ሙሉ ከዚህ በፊት በነበሩ ማሻሻያዎች የታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን ለመሙላት ዘመኑን የሚመጥን የመንግሥት አገልግሎት አሥተዳደር ሪፎርም አስፈላጊ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በአገልግሎት ፈላጊው የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአስተሳሰብ የተገነባ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል።
የተቋማትን አቅም በማጠናከር ተቋማት ባላቸው የልማት አቅም ወጥ በኾነ መልኩ በማደራጀት በውጤታማነት ሊመራ የሚችል ብቃት ያለው እና ዘመናዊ የሰው ኀይል መገንባት ተገቢ ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በሥራ ተነሳሽነት የተገነባ አገልጋይ የሰው ኀይል ማልማት ተገቢ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የመንግሥት አገልግሎት አሥተዳደር ሥርዓቱ ጠንካራ እንዲኾን ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት በየተቋሙ ተናባቢ እና ወጭ ቆጣቢ አደረጃጀት በመዘርጋት ሕዝብ ከሚጠብቀው እና ከለውጡ ፍላጎት ጋር ሊጣጣም የሚችል አገልግሎትን መተግበር ይገባል ብለዋል።
ለአገልጋዩ እና ለተገልጋዩ ቀልጣፋ እና የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ደረጃ ሊፈጽም የሚችል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት የተቋማት አሠራርን በማዘመን ነፃ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን