
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ዛሬ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ጋር በመሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ70 ዓመታት የላቀ የማስተማርና የምዕተ ዓመት የአገልግሎት ጉዞውን በሚዘክርበት ዕለት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መርቀን ከፍተናል ብለዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የካንሰር የጨረር ህክምና ማዕከል፣ የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት፣ ሰው ሰራሽ እግር ማምረቻ፣ የቅድመ ህክምና ቤተ ሙከራ፣ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች፣ ለፈጠራና ምርምር የሚመች የግቢ ልማት እንዲሁም የዲጂታላዜሽን እና ሲስተም አውቶሜሽን ዩኒቨርሲቲው በዕድሜው ልክ ልቆ እንዲወጣ ትልቅ ሚና ያበረክታሉ ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ትናንትን፣ ዛሬና ነገን በማስተሳሰር በአፍሪካ ከምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመኾን የያዘውን ዕቅድ እንዲያሳካ፣ አገልግሎቱን ይበልጥ እያዘመነ እና እያላቀ በትውልድ እና ሀገር ግንባታ አሻራውን እንዲያኖር ጉልህ አበርክቶ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሀገራችንን እንዲሁም የጎንደርን የታሪክ፣ የጥበብ፣ የሥልጣኔ እና የትምህርት ማዕከልነት ማሳያነቱን በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ለማለት እወዳለሁ።
“አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ራዕይን በማሳካት ጎዳና ላይ ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉ ፕሬዝደንት፣ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት፣ አመራሮች እና መላው ማኅበረሰብ፣ የጎንደር ከተማና አካባቢው ሕዝብ ላደረጉልን የደመቀ አቀባበል ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!