የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ኅብረተሰቡ በአረንጓዴ ልማት ሥራ እንዲሳተፍ ጠየቀ።

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም በ2017 ክረምት በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ ማስጀመሪያ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ፎረሙ ስለሠራቸው ተግባራት እና በመጭው ክረምት በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊ የማኅበሩ መሥራች እና አባል ወጣት ምንይችል በላይነህ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ግንዛቤ በመፍጠር፣ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ እየሠራ መኾኑን ገልጿል። በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በከተሞች የኮሪደር ልማትን በአረንጓዴ ልማት የማገዝ ሥራ እንደሚሠሩ ነው ያብራራው።

ወጣት ጌታቸው ማሩ በበኩሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የዓየር ንብረት ለውጥ በመከላከሉ ረገድ የራሳችን ርምጃ ለመውሰድም ጭምር ነው ብሏል። ችግኝ መትከል ብቻም ሳይኾን የሚታየውን የአመለካከት ችግር ለማስተካከል እንደሚሠራም ገልጿል።

ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ተቋማት ድረስ በመተባበር ወጣቶችን በማስተባበር አረንጓዴ ከባቢ የመፍጠር አመለካከት እና ተግባራት እየተሠራ መኾኑንም ነው ወጣት ጌታቸው የገለጸው።

ግሪን ፎረሙ ከጽዱ ኢትዮጵያ ሥራዎች ጋር በመተባበር ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራን ነው ያለው ወጣት ጌታቸው የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁም የተከላ ቦታዎችን በመጎብኘት በመዋቅሩ በኩል እየሠራ መኾኑን አስገንዝቧል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዋሽ እና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ መርሐ ግብር አስተባባሪ ሳሙኤል ከሀሊ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራውን በ2022 ዓ.ም ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ግብ መቀመጡን እና ጤና ቢሮውም ከወጣቶች ፎረም ጋር በመወያየት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ የተሻሻለ መጸዳጃ ቤት እንዲጠቀም እና ጤና ተቋማት ለተገልጋዮች ምቹ እና ሳቢ ለማድረግ በመተባበር እየተሠራ መኾኑንም ነው አቶ ሳሙኤል የገለጹት።

ከወጣቶች ፎረም ጋር በቅንጅት መሥራትን አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል አቶ ሳሙኤል።

የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ፕሬዝዳንት በለጠ ወዳጅነው ፎረሙ ከተመሠረተ 10 ዓመት እንደኾነው ገልጸው ከ15 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉትም ገልጸዋል።

ለክረምት ሥራዎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ፣ ሥምሪት ለመስጠት እና ፕሮግራሞችን ለማስተዋወቅ መድረኩ መዘጋጀቱንም አስገንዝበዋል።

ፍላጎት ያለው ኅብረተሰብ ሁሉ አባል ኾኖ የሚሳተፍበት አሠራር መዘጋጀቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ለውጤታማነቱ የክልሉ መንግሥት እና የተቋማት ድጋፍን እንደሚሻ አሳስበዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዓለም አቀፍ ችግር መኾኑን ገልጸው መንግሥታት በትኩረት እየሠራበት መኾኑን አንስተዋል። ድሃ ሀገራትን በመደገፍ እና ፖሊሲ በማዘጋጀት የአየር ንብረትን መዛባትን ለመቋቋም እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የአማራ ወጣቶች ፎረምም ችግሩን ለመቋቋም ወጣቶችን በማሠባሠብ፣ ግንዛቤ በመፍጠር እና ችግኝ በመትከል አሻራውን ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር ደረጃ ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የጠቀሱት አቶ ጊዜው ኢትዮጵያም ትልቅ እውቅና ያገኘችበት መኾኑን አንስተዋል።

በባሕር ዳር ከተማም መሰል ሥራዎችን ለመፈጸም የውይይቱን አስፈላጊነት ገልጸዋል። ተደጋግፎ በመሥራት ከተማችን ምቹ እና ሳቢ ለማድረግ ከፎረሙ ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል። የከተማው ወጣቶችም ከፎረሙ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ አድርገዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article✍️ የሩጫው ዓለም ጌጥ
Next articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያስገነባቸውን ፕሮጀክቶች መርቀው ሥራ አስጀመሩ።