
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት የሚያስገነባቸው ትምህርት ቤቶች ለ2013 የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ ጎንደር ከተማ አስተዳደር ላይ የተገነባውን የሎዛ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምርህት ቤትን ጨምሮ አራት ትምህርት ቤቶችን በአማራ ክልል እያስገነባ ነው፡፡ የሎዛ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቅቆ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በክልሉ ደቡብ ወሎ ዞን የተገነባው የጦሳ ፈላና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለሥራ ዝግጁ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አስተዳደር ቁልጭ ሜዳና በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሳህላ ሰየምት ወረዳ የሚሠሩት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በታቀደላቸው ዕቅድ ዝግጁ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የሳህላ ሰየምት ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ጥጋቡ ሞላ ለአብመድ እንደገለጹት ትምህርት ቤቱ ጥር 2012 ዓ.ም ጀምሮ 47 በመቶ ገደማ የግንባታ አፈጻጸም ደርሷል፡፡ የሲሚንቶ እጥረት ለግንባታው ፈታኝ እንደሆነበት ግን ተናግረዋል፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ሙሉቀን ፈንታ እንደተናገሩት በጋምቤላ ክልል ከሚገነባው ትምህርት ቤት በስተቀር ሌሎቹ በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የጋምቤላ ክልሉ ግን ዘግይቶ በመጀመሩ አፈጻጸሙ ከሌሎች ዘግይየት ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ ትምህርት ቤቶቹ በ2013 የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ በመዘግየቱ ጥያቄ እየተነሳበት የሚገኘው ትግራይ ክልል ሽሬ ላይ የሚገነባው ትምህርት ቤት እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ወደ ሥራ ሲገባ የኦሮሚያና የትግራይ ክልሎች “በራሳችን እናስፈጽማለን” በማለታቸው ገንዘቡ ለክልሎቹ ገቢ እንደተደረገላቸው አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የሽሬውን ትምህርት ቤት ለማስገንባት ‘‘መስከረም 22/2011ዓ.ም ከክልሉ መንግሥት ጋር ውል ተወስዷል’’ ነው ያሉት፡፡
የትምህርት ቤቱ ግንባታ እንደተጀመረ ሪፖርት እንደተደረገላቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ የሥራው ሂደት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የተደረገው ጥረት አለመሳካቱንም ተናግረዋል፡፡ “ምንም እንኳን እንደተጀመረ ሪፖርት ቢደርሰንም አሁን ላይ ከሕዝብ የሚመጣው ጥያቄ ግን አልተጀመረልንም የሚል ነው” ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ እንደ ሎዛ ብርሃን 2012 ዓ.ም ወደ ሥራ እንደሚገባም ነበር ውል የተያዘው፡፡ አሁን ላይ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ እንዳልተቻለም አስረድተዋል፡፡ ገንዘቡን ግን ለክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ማስገባታቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ከክልሉ ጋር በተደረገው ስምምነትም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚልክና “ከጽሕፈት ቤቱ የሚሄዱትን ሰዎች ወስዶ ያስጎበኛል” የሚሉ ውሎች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ የሽሬውን ትምህርት ቤት በተመለከተ ዳይሬክተሩ እንዳሉት በውሉ መሠረት የማይፈጸም ከሆነ ገንዘቡ ኦዲት ሆኖ ለጽሕፈት ቤቱ እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ እናም ጽሕፈት ቤቱ ራሱ እየተቆጣጠረ ያስገነባዋል፡፡ ለዚህም ደብዳቤ ለክልሉ መጻፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ከክልሉ መንግሥት እስካሁን የመጣ መልስ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ከሚገነቡት መካከል የደቡብ ወሎ ጦሳ ፈላና እና ጎንደር የሎዛ ብርሃን የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ የደባርቅ እና ሰሀላ ሰየምት ወረዳ የሚገነቡት ደግሞ ጥሩ አፈጻጸም ላይ የሚገኙ መሆናቸው ተግልጿል፡፡ ሁለቱም ለ2013 የትምህርት ዘመን እንደሚደርሱ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ጽሕፈት ቤቱ መረጃ የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የሕጻናት ማሳደጊያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 21 የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን እያሠራ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከረጅ ድርጅት ድጋፍ በሚደረግ 716 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ነው እየተገነቡ ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
