✍️ የሩጫው ዓለም ጌጥ

19

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንዶች ከራሳቸው አልፈው ለሀገር የተሰጡ እንቁዎች ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር በአንድ ሰው ምክንያት ሀገር ከፍ ሲል ድንቅ ነገር ነው፤ ከራስ አልፎ ቤተሰብ፣ ሰፈር፣ ክልል እና ሀገር ያስጠራል ያኮራል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የዓለማችን ታላቁ ሯጭ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ግንባር ቀደም ነው።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በረጅም ርቀት ሩጫዎች ያስመዘገባቸው አስደናቂ ውጤቶች፣ የዓለም ክብረ ወሰኖች እና የኦሎምፒክ ድሎች ስሙን በአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም አስፍረውታል። ራሱንም ኾነ ሀገርን እንዲያስጠራ አግዘውታል፡፡

ሰኔ 6 ቀን 1974 ዓ.ም በዚህ ሳምንት አርሲ በቆጅ ከተማ የተወለደው ቀነኒሳ በቀለ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ለሩጫ ልዩ ፍቅር ነበረው። ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ በእግር ኳስ የተወሰነ ጊዜ ቢያሳልፍም፣ የሩጫ ተፈጥሯዊ ችሎታው ይበልጥ ጎልቶ ስለታየ ወደ አትሌቲክስ ሙሉ በሙሉ ፊቱን አዞረ። ቤተሰቦቹም ለአትሌቲክስ ባለው ፍላጎት ትልቅ ድጋፍ አድርገውለታል። ቀነኒሳ ከታላላቅ አትሌቶች አንዱ ለመኾን የበቃው በትጋት፣ በቁርጠኝነት እና በተፈጥሯዊ ችሎታው ታግዞ ነው።

ቀነኒሳ በቀለ በ5 ሺህ ሜትር እና በ10 ሺህ ሜትር ሩጫዎች በርካታ የዓለም ክብረ ወሰኖችን በመስበር እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ስሙን በአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም አስፍሯል።

ከበርካታ ስኬቶቹ መካከል ጥቂቶቹ የአቴንስ 2004 ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ፣ በቤጂንግ 2008 ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር ድርብ ወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል፡፡

አትሌቱ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ቢኾን በ10 ሺህ ሜትር 2003 በፓሪስ፣ 2005 በሄልሲንኪ፣ 2007 በኦሳካ እና 2009 በበርሊን በተከታታይ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ብቸኛው አትሌት ነው። በ5 ሺህ ሜትር 2009 በርሊን ላይም የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል።

የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይም በረጅም ርቀት ሩጫ 2002፣ 2003፣ 2004፣ 2005 እና 2006 በተከታታይ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል።
በአጭር ርቀት ደግሞ 2002፣ 2003፣ 2004፣ 2005 እና 2006 በተከታታይ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል። በዚህ ውድድር በተከታታይ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ከቀነኒሳ በቀር ማንም ያሳካው የለም።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የዓለም ክብረ ወሰኖች መስበር ላይም ስሙ በጉልህ ከሚጠሩ አትሌቶች መሀል ይገኛል በ5 ሺህ ሜትር 2004 በ12:37.35 የዓለም ክብረ ወሰን እና በ10 ሺህ ሜትር በ2004 በ26:17.53 የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቦ የቆየ ሲኾን እነዚህ ክብረ ወሰኖች ለበርካታ ዓመታት ሳይሰበሩም ቆይተዋል።

ከትራክ ሩጫ ወደ ማራቶን በመቀየርም ስኬታማ አትሌት መኾን የቻለው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 2016 የበርሊን ማራቶንን አሸንፏል፡፡ በ2019 በበርሊን ማራቶን ባስመዘገበው 2:01:41ሰዓት የዓለማችን ሁለተኛው ፈጣን የማራቶን ሯጭ ኾኖም ስሙን አስፍሯል።

✍️የጀግንነት ጥግ!

ጀግንነቱ የሀገሩን ክብር በማይጠበቅ ቦታ ገልጿል። በሚያስፈራው መድረክ ሀገሩን አዝሎ የሚመጣውን ሁሉ እስከሞት የደረሰ መሰዋዕትነት ለመቀበል ወስኖም በኃይለኞቹ መድረክ ላይ ተገኘ። ዓላማው የሀገሩን እውነት በመግለጽ በእነሱ መድረክ ላይ ሃሳቡን ሳይፈራ የሚወዳት ሉዓላዊት ሀገር እንዳለችው ለወራሪዎቹ ጣሊያናውያን ነገራቸው ኢትዮጵያዊው ዘርዓይ ደረሰ።

ጀግናው ዘርዓይ ደረሰ በ1908 ዓ.ም ነው የተወለደው። ኢትዮጵያ በጣልያን በተወረረችበት ወቅት፣ በግንቦት 1937 ዓ.ም ገደማ የጣልያንኛ ቋንቋ በመቻሉ ምክንያት በጣልያን ዋና ከተማ ሮም በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞች መካከል እንደ አስተርጓሚ ለመሥራት ነበር በጣሊያን ቀየ የተገኘው።

ዘርዓይ ጣሊያኖች ሰኔ 7 ቀን 1938 ዓ.ም በሮም ፒያሳ ዲ ፒያሜንት በዶጋሊ ጦርነት ለሞቱ 500 ጣልያኖች መታሰቢያ ሕዝባዊ ስብሰባ ያካሂዱ ነበር። ጣልያኖች ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ ለገሀር ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ነቅለው በወሰዱት “የይሁዳ አንበሳ” ሐውልት ዙሪያ ተሰብስበው ሲሳለቁበት እና የኢትዮጵያን ባንዲራ አንጥፈው ሲረግጡት ደረሰ።

በዚህ ጊዜ አልቻለም በድርጊታቸው የተበሳጨው ዘርዓይ ለታሪክ የሚቀመጥ ንግግር ተናገራቸው። “እናንተ ጣልያኖች ነፃነታችሁን ካገኛችሁ ገና ጥቂት ጊዜ በመኾኑና ስለነፃነት የምታውቁት ነገር አንድም ነገር ስለሌለ ነውራችሁን እዚህ በምታደርጉት ተገልጧል” በማለት በቁጣ ተናገረ።

ጀግንነቱንም ለጣሊያናውያን በግልጽ አሳያቸው። በድፍረቱ የተበሳጩት ጣሊያናውያን ብዙ መከራ ቢያበዙበትም ሀገሩ ነጻ እስክትወጣ ግን በጀግንነት ታግሏቸዋል። ከኢትዮጵያ ነፃነት መመለስ በኋላ ዘርዓይ ደረሰ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ተወስኖ በዝግጅት ላይ ሳሉ በድንገት አረፈ ሲሉ ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ “የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

✍️ የነጻነቱ ታጋይ!

ዓለም ላይ ስለነጻነት እና የሀገር ክብር ሲዎራ እና ምሳሌ ሲሰጥ ቀድሞ ስሙ ብቅ የሚለው ኤርኔስቶ “ቼ” ጉቬራ ነው። ይህ ሰው አርጀንቲናዊ ሐኪም፣ ደራሲ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት እና ወታደራዊ መሪ ሲኾን ከ95 ዓመታት በፊት ሰኔ 7 ቀን 1920 ዓ.ም በሮዛሪዮ፣ አርጀንቲና በዚህ ሳምንት ነበር የተወለደው።

በወጣትነቱ የደቡብ አሜሪካ ሀገራትን ሲጎበኝ ያየው ድህነት እና ኢ-ፍትሐዊነት የላቲን አሜሪካ ሕዝብ ከውጭ ሀገር ጭቆና እንዲላቀቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አነሳስቶታል።

ኤርኔስቶ “ቼ” ጉቬራ በጓቴማላ፣ ኩባ፣ ሜክሲኮ እና ቦሊቪያ ፍትሕ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ትግል በማድረግ ነው የሚታወቀው። ከደቡብ አሜሪካ ሀገሮች ውጭም በአልጄሪያና በኮንጎ ነፃነት እንዲረጋገጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ የቻለ ሰው ነው።

✍️ የኔልሰን ማንዴላ የሞት ፍርድ!

ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን ዘረኛ አገዛዝ (አፓርታይድ) ለመቀየር የታገሉ ታላቅ መሪ ናቸው። ትግላቸው የጀመረው በሰላማዊ መንገድ ቢኾንም፣ የጥቁሮች ጭፍጨፋ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች እገዳ ከተጣለ በኋላ ጉዳዩን ለማስተካከል ከፍተኛ ትግልም አድርገዋል።

በ1963 ማንዴላ እና በርካታ ባልደረቦቻቸው ጥፋት ሠርተዋል በሚል ሪቮኒያ በተባለ ቦታ ተይዘው የጥፋት ድርጊት እና መንግሥትን በኀይል ለመጣል በማሴር ተከሰሰዋል። ለእነዚህ ወንጀሎች ደግሞ የሞት ቅጣት ይጠበቅባቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ ማንዴላ እና ባልደረቦቻቸው ላይ የሞት ቅጣት ለመፍረድ እንደተዘጋጀ የተረዱት ማንዴላ እንደፈረንጆቹ ሚያዝያ 20 ቀን 1964 ማንዴላ ታሪካዊ ንግግር አደረጉ። በንግግራቸው መጨረሻ ላይ “ለዚህም ለመኖር ተስፋ አደርጋለሁ፤ ካስፈለገኝም ለመሞት ዝግጁ ነኝ” የሚሉትን የማይረሱ ቃላት ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኔ 11 ቀን 1964 በዚህ ሳምንትም ዳኛው ማንዴላን እና ሰባቱን ባልደረቦቻቸውን ጥፋተኛ ብለው ከፈረዱባቸው በኋላ በማግስቱ ሰኔ 12 ቀን 1964 ሁሉም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ወደ ሮበን ደሴት ከፍተኛ ጥበቃ እስር ቤት ተላኩ። ዴኒስ ጎልድበርግ የተባለው ነጭ ታጋይ ብቻ ግን በተለየ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል።

ማንዴላ ለ27 ዓመታት በእስር ቢቆዩም፣ ትግላቸው ግን አልተቋረጠም። እስራታቸው ለዓለም አቀፍ የአፓርታይድ መለወጥ ትልቅ ማበረታቻ ኾኖ በመጨረሻም የካቲት 11 ቀን 1990 ከእስር ተለቀው የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ፕሬዝዳንት ኾኑ። የኔልሰን ማንዴላን ባዮግራፊን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለታላቁ ዩኒቨርስቲ ታላላቅ ፕሮጀክቶች።
Next articleየአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ኅብረተሰቡ በአረንጓዴ ልማት ሥራ እንዲሳተፍ ጠየቀ።