
ጎንደር፡ ሰኔ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ታላቅ አሻራ ካሳረፉ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ለዓመታት ለሀገር የሚጠቅሙ ምሁራንን አፍርቷል። ሀገር እርሱ በሚያወጣቸው ልጆች ተጠቅማለች። ዛሬም ከዘመኑ ጋር ራሱን እያወዳጀ፣ ለታሪኩ፣ ለአንጋፋነቱ እና ለታላቅነቱ የሚመጥን ሥራ እየሠራ ነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ።
70ኛ ዓመት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ የሚገኘው አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ በጥራት እና በብቃት የገነባቸውን ፕሮጀክቶች ያስመርቃል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) ከወርሃ ጥር 2017 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲውን 70ኛ ዓመት እና የሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በድምቀት ሲያከብሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። የክብረ በዓሉ ማጠናቀቂያ እስከ ሐምሌ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ገደማ ድረስ እንደሚቀጥልም አንስተዋል። እስካሁን በነበሩ ሂደቶች ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል። ነጻ የሕክምና አገልግሎት፣ ነጻ የሕግ አገልግሎት፣ ደም መለገስ እና ሌሎች በርከት ያሉ ተግባራት የበዓሉ ሂደት ኾነው የቆዩ ናቸው።
አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ሲገነባቸው የነበሩ 22 ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግም የበዓሉ አንዱ አካል ነው። በዓሉን ማክበራቸው አጋር አካላት እንዲጨምሩ፣ በመንግሥት እና በሕዝብ ዘንድ የበለጠ አመኔታ እንዲኖር አድርጓል፣ ተጨማሪ ዕድሎች እንዲኖር የሚያደርግም ነው ብለዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መነሻው ማኅበረሰብ ነው፣ ለማኅበረሰብም የቆመ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የማኅበረሰብ አገልግሎት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መገለጫ ነው ብለዋል። ተማሪዎች ሲማሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት በስፋት እንደሚሰጡም ተናግረዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በዐይን ሞራ ግርዶሽ ብርሃናቸውን አጥተው የነበሩ ወገኖችን በነጻ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ብርሃናቸውን መመለሱንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎችን መሥራቱንም ተናግረዋል። የጎንደር ዩነቨርሲቲ የስትራቴጂክ እቅድ አቅዶ እየሠራ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ራዕያችን በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ከኾኑ 10 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዱ መኾን ነው ብለዋል። ራዕዩን ሊያሳኩ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሚመረቁት የልማት ፕሮጀክቶችም የራዕያቸው ማሳኪያ መንገዶች መኾናቸውን ነው ያነሱት።
ዩኒቨርሲቲውን ተመራጭ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ከሚኾኑት 22 ፕሮጄክቶች መካከል አምስቱ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ መሪዎች ጀምረዋቸው የነበሩ መኾናቸውን አንስተዋል። ቀሪዎቹ ግን በእርሳቸው እና በሌሎች መሪዎች ዘመን የተሠሩ ናቸው። በመንግሥት እና በአጋር አካላት የተሠሩት ፕሮጀክቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ ለኢትዮጵያ በተለይም ለአማራ ክልል ሰፊ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል። ከ22 ፕሮጀክቶች መካከል የካንሰር ሕክምና ማዕከሉ ሕሙማን ሕክምናውን ለማግኘት ብዙ ርቀት ያደርጉት የነበረውን ጉዞ ያስቀራል ነው ያሉት።
በርካታ ወገኖች ለሕክምና አገልግሎት ስለሚመጡ ጎንደር እና አካባቢው የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል እንዲኾን ያደርጋል ብለዋል። የአማራ ክልል አጎራባች ክልሎችን ጨምሮ ለከፊል የሱዳን ሕዝብ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የኦክስጅን ፕላንትም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አልፎ ለሌሎች እንደሚተርፍ እና ትልቅ አቅም የፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲውን ለመማር ማስተማር እና ለሥራ ምቹ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲውን አሠራር የሚያዘምኑ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መሥራታቸውንም ገልጸዋል። ፕሮጀክቶቹ ጥራትን በመጨመር፣ አገልግሎትን በማስፋት ዩኒቨርሲቲው የወጠነውን ራዕይ በአጭር ጊዜ እንዲያሳካ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን