ደሴ፡ ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱም ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ለአርሶአደሮች በውርስ፣ በመሬት ኪራይ፣ በስጦታ እና መሰል ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡
አሚኮ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች መሬትን በዘመናዊ መንገድ ወደ ካዳስተር በማስገባታቸው የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ችግሮች መቅረፉን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል መሬት ቢሮ የመሬት አሥተዳደር ካዳስተር ባለሙያ የሽቴ ፈለቀ የክልሉ መሬት አሥተዳደር 126 ወረዳዎች በካዳስተር ሲስተም ውስጥ ገብተው ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የመሬት አሥተዳደሩ መዘመን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ እንደሚገኝ የገለጹት ባለሙያው በርካታ ብልሹ አሠራሮች እንዲቀንሱ ማድረጉንም ነው የጠቀሱት፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አያያዝ እና አጠቃቀም መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ትዕግስቱ ገብረመስቀል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአርሶአደሮች እጅ ከ50 ሚሊዮን በላይ ማሳ ይገኛል ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ሥራ ከ30 ሚሊዮን በላይ ማሳዎች ዘመናዊ አሠራርን በመከተል 2ኛ ደረጃ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።
አቶ ትዕግስቱ እንደገለጹት ቋሚ ደብተር የተሰጣቸው አርሶአደሮችም ማሳቸውን በዋስትና በማስያዝ ብድር ወስደው ከግብርና ውጭ በኾኑ የገቢ ማስገኛ የሥራ መስኮች መሰማራት ችለዋል።
ሥራውም ካልም በተባለ ፕሮጀክት በስምንት ክልሎች እየተተገበረ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን