በማኅበረሰቡ ችግኞችን የማልማት ልምድ እያደገ መጥቷል።

6

ደሴ፡ ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ እና በጀርመን መንግሥታት ትብብር በደቡብ ወሎ ዞን ስድስት ወረዳዎች እየተተገበረ ያለው የደን እና ብዝኀ ሕይወት ልማት ፕሮግራም የበጀት ዓመቱ የ11 ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

 

ፕሮጀክቱ አርሶአደሩ በደን ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ እንዲገነባ በወል መሬት ላይ ለመተግበር ታስቦ የተጀመረ መኾኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የለጋምቦ ወረዳ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አሰፋ በላይ በወረዳው ከ700 ሄክታር መሬት በላይ በመለየት ከ6ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ታቅፈው እየለማ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

 

አርሶአደሮችም በትኩረት እንክብካቤ እያደረጉ እና እስካሁንም በደኑ ውስጥ ባለው ሳር ተጠቃሚ መኾናቸውን አብራርተዋል፡፡

 

የደቡብ ወሎ ዞን ብዝኀ ሕይወት ጥበቃ እና ልማት ፕሮጀክት የተንታ ወረዳ አስተባባሪ አማረ ጆርጋ እስካሁን ከ949 ሄክታር መሬት በላይ ደን በማልማት ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።

 

እየሠሩት ያለው ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡

 

የተደራጁ አርሶአደሮች እንክብካቤ ስለሚያደርጉ ተግባሩ በታቀደለት መንገድ እየሄደ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡

 

የደቡብ ወሎ ዞን አካባቢ እና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ መኮነን እስካሁን ባለው ሂደት አርሶአደሮች በራሳቸው መንገድ ከተከላ እስከ ጽድቀት ድረስ እየተንከባከቡ መኾኑን ገልጸው ይህም ልምድ ሊወሰድበት የሚችል መኾኑን ተናግረዋል።

 

የደቡብ ወሎ ዞን ብዝኀ ሕይወት ጥበቃ እና ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ቢረሳው ማህቶት (ዶ.ር) ለአርሶአደሮች የአቅም ግንባታ ሥራ በመሥራት አርሶአደሮች በቡድን ተደራጀተው እንዲያለሙ እና በውጤት ላይ ተመሥርቶ እየተተገበረ እንደኾነ ነው ያብራሩት፡፡

 

ፕሮጀክቱ በሀገር ደረጃ የመጀመሪያ በመኾኑ ልምዱ ተቀምሮ በሌሎች አካባቢዎች ሊተገበር እንደሚችልም ነው ያስገነዘቡት፡፡

 

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በደን ልማት ላይ የሚሰማራው የኅብረተሰብ ክፍል ችግኞችን የመንከባከብ ልምድ እያደገ መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡

 

ማኅበረሰቡ ከደን ልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ 12ሺህ 500 ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት፡፡

 

ማኅበረሰቡ ችግኞችን የመንከባከብ ልምዱን እያሻሻለ በትኩረት እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለሁለተናዊ ልማት እና ብልጽግና ገቢን በአግባቡ መሠብሠብ ይገባል።
Next articleበኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት 30 ሚሊዮን ማሳዎች ተለክተው ዘመናዊ የይዞታ ማረጋገጫ ተሠርቶላቸዋል።