
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ የተከናወኑ የዕቅድ አፈጻጸሞች አቅርቧል።
የክልሉ ተቋማት ባለፊት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት ከኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ፣ መሠረተ ልማት ዘርፍ፣ ፍትሕና ሰላም፣ ከማኀበራዊ ልማት ዘርፍ አንጻር ያከናወኑትን እቅድ አፈጻጸም የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ በባሕር ዳር ገምግመዋል፡፡
በሰብል ልማት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ106 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ተገኝቷል፤ ይህም የዕቅዱን 87 በመቶ መሆኑ በሪፖርቱ ቀርቧል። በቀጣይ ለመኸር ወቅት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዥ ሂደት እንዲፋጠንና ፍላጎትና አቅርቦት እንዲመጣጠንም ተመላክቷል።
በቀጣዩ የምርት ዘመን በአንድ ሄክታር 22 ነጥብ 8 ኩንታል ላይ የሚገኘውን አማካይ ምርታማነት ወደ 27 ኩንታል ከፍ ለማድረግ እቅድ መያዙም በሪፖርት ቀርቧል።
በየዓመቱ የሚካሄደው የችግኝት መትከል ሥራው ለክልሉ የደን ሽፋን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነም ቀርቧል፤ የክልሉ የደን ሽፋን 14 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱም ተገልጿል።
እንደሪፖርቱ በግብርና ምርምር ዘርፍ በቴክኖሎጂ አቅርቦት በዘጠኝ ወራት 594 የሙከራ ምርምር ቴክኖሎጂዎች ቀርበዋል። የዕቅዱ 97 በመቶ መፈጸሙም ተነግሯል።
በሰብል ምርምር 218 የሙከራ ምርምሮች እንደቀረቡና በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ረገድም 168 የሙከራ ምርምሮች ቀርበው 27 የትግበራ ሥራ መጀመር መቻሉ የተሻለ አፈጻጸም ተብሏል።
በአፈርና ውኃ ምርምር ዘርፍ ደግሞ 68 የሙከራ ምርምሮች መቅረባቸው ተገልጿል።
በንግድና ገበያ ልማት ዘርፍ በዩኒየኖች እና መሠረታዊ ኀብረት ሥራ ማኀበራት በበጀት ዓመቱ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ጉድለት በድርድርና በፍርድ ቤት ተመልሷል፤ የተመለሰው ገንዘብ ከጠቅላላ ጉድለቱ 120 ነጥብ 98 ሚሊዮን ብር ውስጥ 9 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ እንደሆነም ተመላክቷል።
በዘርፉ 69 ሺህ 754 አዲስ የንግድ ምዝገባ ማካሄዱ በጠንካራ ጎንነት ተነስቷል።
በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ዘርፍ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ 677 ሺህ 33 ሰዎች የገንዘብና እህል ድጋፍ መደረጉም ተነግሯል።
በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ሺህ 400 በላይ ባለሀብቶችን በመመልመል ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ፈቃድ በመሥጠት የተሻለ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ቀርቧል።
በቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ ለ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቢታቀድም 597 ሺህ 930 ብቻ ሥራ ይዘዋል። የዕቅዱ 54 በመቶ ብቻ ነው፤ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች 63 ነጥብ 7 ከመቶ ቋሚና 36 ነጥብ 3 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ነው የተፈጠረላቸው፡፡
ባለፉት 9 ወራት ለ28 ሺህ 808 ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር መፈጠሩ ደግሞ የተሻለ አፈጻጸም እንደሆነ በሪፖርቱ ቀርቧል።
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
