“በአንድ ጊዜ የምለግሳት ደም ቢያንስ የ3 ሰዎችን ሕይወት ትታደጋለች”

16

ደብረብርሃን፡ ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ወቅት በጤና ተቋማት የሚያስፈልገው የደም መጠን አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር ባለመጣጣሙ በሕክምና ሂደቱ ላይ እንከን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

 

ችግሩን ለማቃለል ብሎም ለመሻገር ደም የመለገስ ባሕልን ማጎልበት የግድ ይላል፡፡

 

የደም ባንክ ተቋማት በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት በሕክምና ሂደት ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር በርካታ ናቸው፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የኾነ የደም እጥረት እንዳለ ይነገራል፡፡ ፍላጎት እና አቅርቦቱ የተጣጣመ እንዲኾን ታዲያ በቋሚነት ደም የሚለግስ በጎ ፈቃደኛ ወገን አስፈላጊ ነው፡፡

 

ወጣት ዓለማየሁ ሸዋንግዛው ለ38ኛ ጊዜ ደም ለግሷል፡፡ ለዚህ በጎ ተግባር ያነሳሳው ደግሞ በሚተካ ደም የማይተካውን የሰው ልጆች ሕይወት መታደግ እንደሚቻል መገንዘቡ እንደኾነ ነው የሚገልጸው፡፡

 

ወጣት ዓለማየሁም ደም በመለገሱ የብዙዎችን ሕይወት መታደግ እንደቻለ ነግሮናል፡፡

 

“የጓደኛችን እናት ደም በሚያስፈልጋት ጊዜ ፈጥነን የሄድነው ወደ ደብረብርሃን ደም ባንክ ነበር” ያለው ወጣት ዓለማየሁ መሰል ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ ደም መለገስን ባሕል ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡

 

ወጣት ሰለሞን ከበደ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ ደም በመለገስ አርዓያነት ያለው ተግባር እየፈጸመ ነው ያገኘነው፡፡ ወጣት ሰለሞን እንደሚለው በአንድ ጊዜ የምለግሳት ደም ቢያንስ የ3 ሰዎችን ሕይወት ትታደጋለች፡፡

 

ይህንን በማድረግ የብዙዎችን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል በማመንም በየሦስት ወራት ልዩነት በቋሚነት ደም ይለግሳል፡፡

 

ወጣቶቹ ደም በመለገሳቸው የጎደለባቸው ነገር የለም፤ ይልቁንም የብዙዎችን ሕይወት ማትረፍ በመቻላቸው ደስታቸው ወደር አልባ ነው፤ ሌሎችም የእነሱን አርዓያ እንዲከተሉ ወጣቶቹ ጠይቀዋል፡፡

 

ከደብረብርሃን ደም ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ባሉት የበጀት ዓመቱ ጊዜያት ከ8ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ተሠብሥቧል፡፡

 

ከአጠቃላዩ ደም ለጋሾች መካከል 49 በመቶ የሚኾኑት በቋሚነት ደም የሚለግሱ ናቸው፡፡ አሁን ላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ደም የመለገስ ባሕል እያደገ መምጣቱንም የደብረብርሃን ደም ባንክ አገልግሎት ሥራ አሥኪያጅ በዛብህ ዓባይነህ ነግረውናል፡፡

 

በጤና ተቋማት ከፍተኛ እጥረት ላለባቸው የደም ዓይነቶች የለጋሾች ቡድን በማቋቋም አቅርቦቱን ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን ነው ሥራ አሥኪያጁ የገለጹት፡፡

 

“O” ኔጌቲቭ፣ “A” ኔጌቲቭ፣ “AB” ኔጌቲቭ እና “B” ኔጌቲቭ የመሳሰሉ የደም አይነቶች ከፍተኛ እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

 

ይህንን እጥረት ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማስቀረትም እንደየደም አይነቶቹ የለጋሾ ቡድን የማቋቋም ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት፡፡

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

  1. https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበገንዳ ውኃ ከተማ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ከፍት ኾነ።
Next articleአንፃራዊ ሰላሙ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲሸጋገር የሰላም ግንባታ ሥራዎች መቀጠል ይገባቸዋል።