በገንዳ ውኃ ከተማ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ከፍት ኾነ።

13

ገንዳ ውኃ፡ ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

 

በምረቃ መርሐ ግብሩም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የአካባቢው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት መከፈቱን ተናግረው የተሠራው በከተማ አሥተዳደሩ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ መኾኑንም ተናግረዋል።

 

የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቱ መከፈቱ ለከተማው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን ለአጎራባች ቀበሌዎችም ጭምር የሚጠቅም ተግባር ነው ብለዋል።

 

ማኅበረሰቡ በመድኃኒት እጥረት ምክንያት እንዳይንገላታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚያስችለውም አስገንዝበዋል።

 

የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲስተር ምግብ ፈንታ በጤናው ዘርፍ ማኅበረሰቡ የሚያነሳውን የመድኃኒት እጥረት ጥያቄ ለመፍታት አንዱ መፍትሔ ተብሎ የተወሰደው የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት እንደኾነ ገልጸዋል።

 

የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቱ መከፈት በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።

 

በከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በተሠበሠበ 2 ሚሊዮን ብር የመድኃኒት ግዥ ተፈጽሞ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

 

በከተማው የተሠራው የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ለሌሎች ከተሞች እና ወረዳዎች ተሞክሮ እንደሚኾንም ኀላፊዋ ገልጸዋል።

 

በቀጣይ ማኅበረሰቡ ይህን ጥሩ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

 

በምረቃው ላይ የተገኙት መምህር ዳኛው አዲስ ማኅበረሰቡ በጤናው ዘርፍ ላይ እንደከተማ እያጋጠመው ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት የሚቀርፍ ተግባር ነው የተሠራው ብለዋል። ተግባሩም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት።

 

ቀጣይም ሌሎች የመድኃኒት ቤቶች እንዲከፈቱ ማኅበረሰቡ ተሳትፎውን እና ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ነው ያሉት።

 

ሌላኛዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ብዙየ የሱፍ ማኅበረሰቡ ጤና ጣቢያ ሂዶ አገልግሎቱን ያገኛል ነገር ግን የመድኃኒት እጥረት ይገጥመው ስለነበር አሁን የተከፈተው የማኅበረሰብ መድኀኒት ቤት ችግሩን ይፈታል ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

 

ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረውም መንግሥት ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግም ነው የጠየቁት።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ለእናቶች ማቆያ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ድጋፍ አደረገ።
Next article“በአንድ ጊዜ የምለግሳት ደም ቢያንስ የ3 ሰዎችን ሕይወት ትታደጋለች”