ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ማዘንጊያ እንዳሉት ማኅበሩ በእናቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አፍላ ወጣቶች እና በቤተሠብ ጤና ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በመቅጠር እና ሥልጠናዎችን በመሥጠት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሠጡ እያደረገ የሚገኝ የሙያ ማኅበር ነው።
ባለፋት 20 ዓመታት በእናቶች ጤና ላይ በተሠራው ሥራ የእናቶች ሞት መቀነሱን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በጦርነት ወቅት የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ማኅበሩ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ጋር በመተባበር ባለሙያዎች ገብተው እንዲሠሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በእናቶች ማቆያ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ ሠርቷል። አሁን ላይም ለሁለት ጤና ጣቢያዎች ለሚገኙ የእናቶች ማቆያ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የመመገቢያ ቁሳቁሶች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የመኝታ አልጋዎች፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች እና ሌሎች ግብዓቶችን ድጋፍ አድርጓል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ
ሕዝብ ፈንድ ድርጅት የአማራ ክልል ተወካይ ጌቱ ቸርነት በኢትዮጵያ የእናቶች እና የወጣቶች አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና እንዲሻሻል እና መብቶቻቸው እንዲጠበቁ ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል።
በተለይም ደግሞ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ደግሞ የቤተሰብ ምጣኔ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የግብዓት ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ ዶክተር ቤተልሄም መኮንን እንዳሉት በክልሉ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ የእናቶች ማቆያ ማሟላት አንዱ ነው። በክልሉ አሁን ላይ ከ700 በላይ የእናቶች ማቆያ ቢኖሩም ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ አገልግሎት እየሠጡ የሚገኙት ከ500 አይበልጡም ብለዋል።
በእነዚህ ተቋማት ቢሮው ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። አሁን ላይ የተደረገው ድጋፍም የማስፋፊያ ግንባታ ተገንብቶላቸው ቁሳቁስ ያልተሟላባቸውን ማቆያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያደርግ መኾኑን አንስተዋል። የእናቶችን ሞት ለመቅረፍ ሌሎች አጋር አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ኃይለኢየሱስ ዳኘው በዞኑ በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት እናቶች እና ሕጻናት ተጎጅ መኾናቸውን አንስተዋል። ድጋፉ የእናቶችን ሞት ለመቅነስ ለተያዘው መርሐግብር አቅም የሚሠጥ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን