
ፍኖተ ሰላም: ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፈጠነች ኡስማን እና ፀሐይነሽ በላይነህ በቡሬ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው።
ለአሚኮ እንዳሉት ከዚህ በፊት መጓደል የነበረበት የግቢ ፅዳት፣ የባለሙያ እጥረት እና የግብዓት ችግሮች አሁን ላይ ተሻሽሏል ብለዋል። አሁንም ግን አንዳንድ ክፍሎች ላይ የባለሙያ እጥረት ቢስተካከል የተሻለ አገልግሎት ማግኘት እንችላለን ብለዋል።
በጤና ጣቢያው ውስጥ በእናቶች ክፍል የባለሙያ እጥረት በመኖሩ በርካታ እናቶች ሪፈር ይባሉ የነበረ መኾኑን የገለጹልን ደግሞ በቡሬ ጤና ጣቢያ አዋላጅ ነርስ አድባሩ ዋለ አሁን ግን ተገቢውን አገልግሎት ለእናቶች እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል።
በጤና ጣቢያው ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመለየት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ደምሴ ተናግረዋል።
በዚህም ተቋሙን ለተገልጋዮች ምቹ፣ ፅዱ እና ማራኪ ማድረግ እና በግብዓት የማሟላት ሥራ መሠራቱን አንስተዋል። አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳለጥ የሰው ኀይል እጥረቶችንም ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዞኑ ባሉ የጤና ተቋማት የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ተቋማትን ለተገልጋዮች ምቹ እና ጽዱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ክፍሌ ተናግረዋል።
በየጊዜው አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት እና ችግሮችን በመለየት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በዚህም የቡሬ ጤና ጣቢያ አንዱ መኾኑን ጠቁመው ይህንንም ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት የማስፋት ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ኀላፊው አክለው የጤና ተቋማትን ጽዱ እና ለተገልጋዮች ምቹ ከማድረግ ባለፈ በግብዓት የማሟላት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የጤና ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች የቡሬ ጤና አጠባበቅ ጣቢያን ጎብኝተዋል።በጉብኝቱ የተሳተፉ የጤና ተቋማት እና ሠራተኞችም ጥሩ ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!